የኢራን ልኡካን ቡድን ሳዑዲ አረቢያ ገባ

የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ኻሚኒ (ፎቶ ፋይል AP)

በባሕረ ሠላጤው ባላንጣ አገሮች - በሳዑዲ አረቢያ እና በኢራን መሀከል ያለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማደስ እና ከሰባት ዓመት በፊት ወደ ነበረበት ለመመለስ፣ የኢራን ልኡካን ቡድን አባላት፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባታቸውን ቴህራን አስታወቀች፡፡

ይህ የተገለጸው፣ የሳዑዲ አረቢያ የልኡካን ቡድን፣ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ተመሳሳይ ጉብኝት ማድረጉ ከተነገረ ከጥቂት ቀናት በኋላ መኾኑን፣ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ጉብኝቱ የተደረገው፣ የኹሉቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ሁከት በሰፈነበት ክልል መረጋጋትን ለማምጣት፣ ቻይና ውስጥ በተካሔደው ስብሰባ ቃል ከገቡ በኋላ ነው፡፡

የኢራን ልኡካን፥ በሪያድ የሚገኘውን ኤምባሲ እና በጅዳ ያለውን ቆንስላ ጨምሮ፣ በጅዳ የኢራን ቋሚ ተጠሪ የሚያደርጓቸውን የእስላማዊ ትብብር ሥራዎችን ለማስቀጠል፣ አስፈላጊውን ርምጃ ኹሉ ይወስዳሉ፤ ሲሉ፣ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናሳር ካናኒ በአወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴው እየተሟሟቀ የመጣው፥ በመከካለኛው ምሥራቅ አካባቢ የሚካሔዱ ግጭቶችን ከአንዱ እና ከሌላው ወገን እየኾኑ ይደግፋሉ፤ የሚባሉት ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ፣ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማደስ ባለፈው ወር መስማማታቸውን፣ አደራዳሪዋ ቻይና ከአስታወቀች በኋላ ነው፡፡