ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመውን፣ የነፍስ አድን ርዳታ ዝርፊያ ጉዳይ እየመረመረ መኾኑን፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡ “የርዳታ እህል ከፍተኛ ሽያጭ የሚታይባቸው ገበያዎች አሳስበውኛል” ያለው ድርጅቱ ለ100 ሺሕዎች የሚበቃ የርዳታ እህል ከሽራሮ መጋዘኑ መዘረፉን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ርዳታ ፕሮግራም(WFP) ይህን ያስታወቀው፣ ከቀናት በፊት ለአጋሮቹ በጻፈውና አሶሽየትድ ፕሬስ ከእጁ መግባቱን ይፋ በአደረገው ደብዳቤ ነው። ባለፈው ረቡዕ፣ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አጋር ለኾኑ ድርጅቶች የተላከ ነው።
አሶሽየትድ ፕሬስ ደብዳቤውን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቢሮ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር፣ በአንዳንድ ገበያዎች የሚታየው ከፍተኛ መጠን ያለው የርዳታ እህል ሽያጭ፣ ድርጅታቸውን በእጅጉ እንዳሳሰበው አመልክተዋል፡፡
ጃቢዳር አያይዘውም፣ “ከታለመበት ዓላማ ውጭ ስለዋለ የርዳታ ምግብ፥ በሠራተኞቻችኹ፣ በተረጂዎች አልያም በአካባቢው ባለሥልጣናት አማካይነት የደረሳችኹ መረጃ ካላችኹ አካፍሉን፤” ሲሉ አጋሮቻቸውን ጠይቀዋል።
ደብዳቤው፥ ምንም ዓይነት ተለይተው የተረጋገጡ ወይም የደረሰባቸውን ግኝቶች አይጠቅስም። ይኹንና የተዘረፈው የርዳታ እህል መጠን፣ ለ100 ሺሕ ሰዎች የሚበቃ ምግብን እንደሚጨምርና በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ክፉኛ በተጎዳችው የሽራሮ ከተማ ከሚገኝ መጋዘን ስለ መወሰዱ በቅርቡ እንደተደረሰበት፣ ከጉዳዩ አሳሳቢነት የተነሣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ኹለት የረድኤት ሠራተኞች እንደገለጹለት ዘግቧል።
ቀጣናውን ክፉኛ በመታው ድርቅ እና ረኀብ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ግጭት ከጠቅላላ ሕዝቧ 20 ሚሊዮኑ የርዳታ ምግብ ጠባቂ በኾነባት ኢትዮጵያ ይህ ድርጊት መፈጸሙ፣ “የድርጅቱን ስም ማጉደፍ ብቻ ሳይኾን፣ አፋጣኝ እገዛ ለሚሹ ሰዎች የመድረስ ዐቅሙን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤” ብለዋል ዳይሬክተሩ ክላውድ ጂቢዳር።
ዳይሬክተሩ አክለው እንዳሳሰቡት፣ በአገሪቱ የሚታየውን፣ በሰብአዊ ርዳታ ላይ የሚፈጸም ምዝበራ እና ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለማዋል የሚደረግ ሙከራ ለመግታት አፋጣን ርምጃ መወሰድ ይኖርበታል።