የቤቶች ፈረሳው መኖሪያ አልባ ዜጎችን እንዳያበራክት ኢሰመኮ አሳሰበ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) አርማ። ከፌስቡክ ገፃቸው ላይ የተወሰደ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) አርማ። ከፌስቡክ ገፃቸው ላይ የተወሰደ።

በኦሮሚያ ክልል፣ ዐዲስ በመመሥረት ላይ በሚገኘው በሸገር ከተማ በተፈጸመው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማንሣት ርምጃ የተጎዱ ሰዎች፣ በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ።

ኮሚሽኑ፣ ዛሬ ምሽት በአወጣው መግለጫ፣ “ተጎጂዎቹ ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች ይገባል፤” ብሏል፡፡

መኖርያ ቤቶችን የማፍረስ ርምጃው፣ “ኢትዮጵያ ያጸደቀችውን ዓለም አቀፍ ሕግ በተፃረረ መንገድ” እየተፈጸመ እንደሚገኝ የጠቆመው ኮሚሽኑ፣ ይህም የቤት አልባ ነዋሪዎችን ችግር እንዳባባሰ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ በዐዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ፣ በቅርቡ በዐዲስ መልክ በተደራጀው የሸገር ከተማ አስተዳደር፣ የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ የማሥነሳት ርምጃ እየተከናወነባቸው በሚገኙ አካባቢዎች፣ ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትል እና ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ዛሬ ምሽት በአወጣው መግለጫ፣ “የቤት ማፍረሱ እና በግዳጅ የማሥነሳቱ ተግባር፣ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንደነበረና በቦታው ከፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ፣ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም አረጋግጫለኹ፤” ብሏል፡፡

ይህንም፣ ለኮሚሽኑ ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎችን፣ የሚመለከታቸውን የከተማ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት በማነጋገር እንዲሁም በለገጣፎ ለገዳዲ፣ በሰበታ አካባቢ ፉሪ እና ለቡ ተክለ ሃይማኖት እንዲሁም፣ በቡራዩ ገፈርሳ ኖኖ አካባቢዎች፣ የመስክ ምልከታ በማድረግ በአሰባሰበው መረጃ እና ማስረጃ ማረጋገጡን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ ርምጃው ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር እንደኾነም አብራርቷል፡፡

ሕገ ወጥነቱን ሲያስረዳም፣ “ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት፣ ያለበቂ ማስጠንቀቂያ የተከናወነ፣ አድሎአዊ ርምጃ ነው፤” ብሏል፡፡በተጨማሪም፣ ቤቶችን በማፍረስ ሒደት፥ እስር፣ የአካል እና ሥነ ልቡናዊ ጉዳት እና እንግልት መድረሱን ጠቅሷል፡፡

ፊሊዶሮ በተባለ ቦታ ላይ በተደረገ የቤት ፈረሳ፣ የሰው ሕይወት ስለ ማለፉ መረጃ እንደደረሰው የጠቀሰው ኢሰመኮ፣ ይኹን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ፣ “ከፖሊስ ጋራ በነበረ ግጭት መጠነኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ የሞተ ሰው ግን የለም፤” ማለቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ ይህን በተመለከተ፣ ተጨማሪ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

ከእስር ጋር በተያያዘም፣ ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ፣ “የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፤” ብሏል፡፡

“የማፍረስ እና በግዳጅ የማንሣት ርምጃው፣ በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ ኢኮኖሚዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓል፤ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ለማቋረጥ ተገደዋል፤ በርካታ ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ኹኔታ ተፈጥሯል፤ በርካታ ቤተሰቦች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሔድ ተገደዋል፤ ከፊሎቹም ጎዳና ላይ ወድቀዋል ወይም በተለያዩ የሀገር ውስጥ መጠለያ ጣቢያዎች በመሰብሰብ የመንግሥት ርዳታ ለመጠባበቅ ተገደዋል፤” ሲልም ኮሚሽኑ የችግሩን ጥልቀት አትቷል፡፡

“ስለኾነም፣ በማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሣት ርምጃው ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ እና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች ይገባል፤” በማለት አሳስቧል፡፡

የኢሰመኮ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረ ሚካኤል፣ “ሕጋዊነትን ያልጠበቁ ይዞታዎችን መከላከል የመንግሥት ሓላፊነት ቢኾንም፣ የማፍረስ እና በግዳጅ የማንሣት ርምጃዎች፣ ሰዎች ሕይወታቸው እንዲናጋ እና ቤተሰብ እንዲበተን የሚያደርግ ሊኾን አይገባም፤ ይልቁንም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የተጠበቁበት አሠራር መኾኑን ማረጋገጥ ይገባል፤” ማለታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡