-
የሥራ ሥምሪቱን የሚቆጣጠር አካል እና አሠራር አስፈላጊነት
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪትን ከማመቻቸት ጎን ለጎን፣ ሒደቱን የሚቆጣጠር አካል ማቋቋም እና አሠራሩን መዘርጋት እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕፃናት እና ሴቶች መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገሥጥ፣ መንግሥት ሠራተኞችን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የመላኩን ሥራ ማመቻቸቱ በበጎ የሚታይ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ኾኖም፣ “ሒደቱን የሚቆጣጠር አካል እና አሠራር ያስፈልገዋል፤” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በርካታ ዜጎች ኢመደበኛ እና ሕገ ወጥ በኾነ መንገድ ወደተለያዩ አገሮች በሚያደርጉት ጉዞ፣ ለልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደሚጋለጡ ገልጾ፣ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ፣ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪቱን በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በአወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሠራተኞች በብዛት እንደሚጓዙበት ከሚጠቀሱ አገሮች ቀዳሚዋ ሳዑዲ አረቢያ ናት፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት፣ ከኢትዮጵያ የቤት ሠራተኞችን ለመቅጠር ያሳለፈውን እገዳ ከሦስት ዓመት በኋላ ቆይታ አንሥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በሳዑዲ አረቢያ በሚኖራቸው የሥራ ሥምሪት፣ የተሻለ የሥራ ክፍያ የሚያስገኝላቸውን ድርድር ከሳዑዲ መንግሥት ጋራ ማድረጉን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ይህን ተከትሎም የሳዑዲ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ወርኀዊ የቅጥር ክፍያ ከፍተኛ ጣሪያ ነው ያለውን የ6ሺሕ900 ሪያል(1ሺሕ800ዶላር) መመደቡን አስታውቋል፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚመጡ ሠራተኞችን እንደሚቀበል እና እንደሚያበረታታም በሰሞኑ መግለጫው አስገንዝቧል፡፡
የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪትን ማመቻቸት መጀመሩን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ዜጎች የውጭ ሀገራት የሥራ ዕድሎችን በአገባቡ እንዲጠቀሙ መክሯል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5