በአፍሪካ ቀንድ ለስድስተኛ ተከታታይ ወቅት ዝናብ ላይጥል እንደሚችል በመገመቱ በቀጠናው አስከፊው ድርቅ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ተቀስቅሷል። የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች የጋራ ልማት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ እና በቀጠናው የአየር ንብረትን የሚቆጣጠር አንድ ተቋም ትላንት ዕረቡ ባወጡት ማስጠንቀቂያ ይጥላል ተብሎ ከሚጠበቀው በእጅጉ ያነሰ ዝናብ ስለሚኖር አስከፊውን ድርቅ የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችል አመላክተዋል።
ከአስር አመት በፊት በሶማሊያ ብቻ 260 ሺህ ሰዎች ከሞቱበት የከፋ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ሲልም ስጋቱን ገልጿል። የአየር ትምበያዎች በዚህ በያዝነው የ2015 ዓ.ም ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው የዝናብ ወቅት መጣል የነበረበት ዝናብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ እና ከፍተኛ ሙቀት እንደሚኖር ማመላከታቸውን የልማት፣ አየር ትንበያ እና አፈፃፀም ማዕከል በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ICPAC) አስታውቋል።
በአብዛኛው የአፍሪካ ቀንድ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ወሳኝ የዝናብ ወቅት ከዓመታዊ አጠቃላይ የዝናብ መጠን እስከ 60 በመቶውን የሚሸፍን ሲሆን ፤ ሁኔታው ሚቲኦሮሎጂ ባለሞያዎች እና የእርዳታ ተቋማት በቀጠናው ለረጅም ግዜ በቆየው አስከፊ ድርቅ ሳቢያ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያጋጥም ይችላል ሲሉ ያስጠነቀቁትን ፍራቻ የሚያረጋግጥ ነው።
አይፓክ በመግለጫው "ድርቁ ባጠቃቸው የተወሰኑ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ዩጋንዳ አካባቢዎች ዝናብ ለስድስተኛ ተከታታይ ወቅት ላይጥል ይችላል" ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲኦሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ ባለፉት ተከታታይ ወቅቶች በድርቅ ተጠቅተው ከቆዩ አካባቢዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከመደበኛ በታች የሆነ የበልግ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ትንበያ አስቀምጧል።
በሌላ በኩል አክሽን አጌንስት ሀንገር የተሰኘው በአፍሪካ ቀንድ ረሃብን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ርዳታ ሰጪ ተቋም የኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር ቤዛ አበበ በኢትዮጵያ እስካሁን 12 ሚልየን ሰዎች ለሞት ለሚዳርግ የድርቅ አደጋ መጋለጣቸውን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ለስድስተኛ ተከታታይ ወቅት ዝናብ ሙሉ ለሙሉ ላይጥል እንደሚችል ያረጋገጡት ቤዛ አበበ ሁኔታው ላለፉት አምስት ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት በከፋ ሁኔታ እንደሚያባብሰው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ እየተባባሰ ላለው አስከፊ ድርቅ አስቸኳይ እና ተመጣጣኝ ምላሽ ካልተሰጠ ድርቁ ወደ ረሃብ አደጋ ሊቀየር እንደሚችልም ወይዘሮ ቤዛ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ቦረና ውስጥ ድርቅ መበርታቱንና ነዋሪዎቹ በምግብ እጥረት መቸገራቸውን ከዚህ ቀደም ወደ ስፍራው ተጉዞ ለነበረ የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ መናገራቸው ይታወሳል። ወደ ስምንት መቶ ሺህ የሚሆን ሰው የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው፣አዛውንቶችና ሕፃናት በረሃብ እየተጎዱ መሆናቸውና የሚደርሰው የእርዳታ እህልም እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር እንዲሁም ደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች ና ህዝቦች ክልል ላለፉት ሁለት ዓመታት በድርቅ በመጠቃታቸው ቁጥራቸው የበዙ ሰዎች እርዳታ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች መናገራቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ አሁንም በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ አፋር፣ ደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንዳ በድሬደዋ የከተማ አስተዳደር ከ11.8 ሚልዮን በላይ ሕዝብ በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አስታውቋል።
አይፓክ ባወጣው መግለጫም "ድርቁ ባጠቃቸው የተወሰኑ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ዩጋንዳ አካባቢዎች ዝናብ ለስድስተኛ ተከታታይ ወቅት ላይጥል ይችላል" ብሏል።
የአፍሪካ ቀንድ ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም ተጋላጭ ከሆኑ ቀጠናዎች አንዱ ሲሆን ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በተደጋጋሚ እና በከፍተኛ መጠን እየተከሰቱ ነው። ላለፉት 5 ተከታታይ ወቅቶች ያልጣለው ዝናብ በሚሊየን የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችን ገድሏል፣ ሰብሎችን አውድሟል፣ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ ምግብ እና ውሃ ፍለጋ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።