“ሩሲያ የወታደር እጥረት ገጥሟታል” - እንግሊዝ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ AP (02.11.23)

ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበት አንደኛ ዓመት በተቃረበበት በዚህ ወቅት፣ በቂ ወታደሮችን በመመልመል ረገድ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟታል ሲል የእንግሊዝ የመከላከያ ሚኒስቴር በዕለታዊ የመረጃ ሪፖርቱ አስታውቋል።

ዋግነር ግሩፕ በመባል የሚታወቀው ከእስር ቤቶች ወታደሮችን የሚመለምለው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ምልመላውን ማቆሙን ካስታውቀ በኋላ ሩሲያ አስቸጋሪ አማራጮች ከፊቷ ተደቅነዋል ብሏል የእንግሊዙ የመከለአከያ ሚኒስቴር በመግለጫው።

“ያሏትን ወታደሮች አሟጦ መጠቀም፣ የያዘቻቸውን እቅዶች መቀነስ ወይም ሌላ ተጨማሪ ምልመላ ማድረግ” ሩሲያ ከፊቷ ያሉ አማራጮች ናቸው ብሏል የእንግሊዙ የመከላከያ ሚኒስቴር።

ታሳሪዎች በጦርነቱ በመሳተፍ ከእስር ለመለቀቅ የነበራቸው ጉጉት ቀንሷል።ይህም በዩክሬን የሚገጥማቸው ዕጣ-ፈንታ እስር ቤት ባሉት ዘንድ ግልጽ እየሆነ በመምጣቱ ነው ሲል መከላከያ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አክሏል።

ዋግነር የተሰኘው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ምልመላውን ያቆመው ከሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ‘እኔ እበልጥ’ ፉክክር ውስጥ በመግባቱ ሳይሆን እይቀርም ሲል የእንግሊዙ የመከላከያ ሚኒስቴር ግምቱን አስቀምጧል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሳምንት በኋላ ወደ ፖላንድ በማቅናት ከሃገሪቱ ፕሬዝደንትና ከምሥራቅ አውሮፓ ሸሪኮቻቸው ጋር እንደሚወያዩ ዋይት ሃውስ ትናንት ዓርብ አስታውቋል።