"አሜሪካ በአፍሪካ ፍላጎት ላይ አትወስንም" - ብሊንከን

Your browser doesn’t support HTML5

" አሜሪካ በአፍሪካ ፍላጎት ላይ አትወስንም" - ብሊንከን

ዩናይትድ ስቴትስ ለሶስት ቀናት በዋሽንግተን ዲሲ ስታስተናግደው የቆየችው የአሜሪካ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በትላንትናው እለት ሲጠናቀቅ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አሜሪካ በአፍሪካ ፍላጎት ላይ እንደማትወስንና፣ ሌላ የትኛውም ሀገርም ሊወስን እንደማይገባ ተናግረዋል። አሜሪካ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር የሚኖራት ግንኙነት ምን እንደሚመስልም ጠቅለል አርገው አብራተዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ ለሶስት ቀናት የተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ከንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብሮች አንስቶ እስከ ዲሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የተነሱበት ሆኖ ተጠናቋል። በጉባዔው ላይ አፅንኦት የተሰጠው ጉዳይም፣ አሜሪካ ለአፍሪካ ምን መስራት ትችላለች ሳይሆን፣ ከአፍሪካ ጋር ምን መስራት እንችላለን የሚለው መርሆ እንደሆነም የአሜሪካ ከፍተኛ አመራሮች ገልፀዋል። በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አንተኒ ብሊንከንም ይህንኑ ነው አፅንኦት ሰጥተው ያብራሩት።


"አስፈላጊ የሆኑ ውይይቶች በሚካሄዱበት እና ውሳኔዎች በሚወሰኑበት ማንኛውም ጊዜ የአፍሪካ ሀገራት በጠረጴዛ ዙሪያ ትልቅ ቦታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ቁርጠኞች ነን። በመስከረም ወር በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያንን አሳይተናል። ፕሬዝዳንት ባይደን አፍሪካ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል እንድትሆን ድጋፋቸውን ሲገልፁ ሰምታችኃል። በዚህ ሳምንት ደግሞ ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ህብረት የቡድን 20 ቋሚ አባል ሀገር እንዲሆን ድጋፋቸውን አስታውቀዋል።"


ዩናይትድ ስቴትስ በመጪዎቹ ሶስት አመታት በአፍሪካ ሀገራት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል 55 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ይፋ አድርጋለች። ይህ የገንዘብ ድጋፍ ግን በትብብር ለሚሰሩ ስራዎች እንደሚውል ብሊንከን አመልክተዋል።


"ለምንኖርበት ፕላኔት ግልፅነት፣ ከፍተኛ ጥራት እና ዘላቂነት ያለው መዋዕለ ነዋይን ነው ያቀርበብነው። በየሀገሮች ያሉ ማህበረሰቦችን እናበረታታለን። የህዝቦችን መብት እናከብራለን፣ ህዝቡን እናዳምጣለን፣ ፍላጎቱን እንሰማለን። አሜሪካ በአፍሪካ ፍላጎት ላይ አታዝም፣ ሌላ ማንም ቢሆን ማዘዝ የለበትም።"


ብሊንከን በመግለጫቸው ዓለም አቀፉን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል አሜሪካ የአፍሪካ ቀዳሚ አጋር እንደነበረች አስታውሰዋል።

"የጤና ደህንነትን በተመለከተ 231 ሚሊየን ጠብታ የሚሆኑ አስተማማኝ እና ውጤታማ የኮቪድ 19 ክትባቶችን ለአፍሪካ ሀገሮች በነፃ ሰጥተናል።"

ብሊንከን አክለው በምግብ እጦት እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ዙሪያ መንግስታቸው ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረገ አብራርተዋል።

"በምግብ እጦት ዙሪያ ባለፈው አመት የዓለምን ረሃብ ለመቅረፍ እና የተመጣጠነ ምግብ ለማሻሻል የሚውል ከ11 ቢሊየን ዶላር በላይ ሰጥተናል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ገንዘብ ባልተመጣጠነ መልኩ ረሃብን በሚያፋጥኑ እንደ ኮቪድ፣ የአየርን ብንረት ለውጥ፣ ግጭት እና ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ በሚያካህደው ጦርነት ተፅእኖ ወደደረሰባቸው የአፍሪካ ሀገሮች ነው የሄደው።"

ከሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ አሜሪካ የአየር ንብረት ለውጥን መታደግ በሚያስችሉ ታዳሽ ኃይሎች ዙሪያ ድጋፍ እንደምታደርም ገልፀዋል።

"ከዚህ አመት መጀመሪያ ጥር ወር ጀምሮ ብዙ ሀብቶችን ለዚህ አላማ እንዲውል ሰጥተን። ለአንጎላ ከፀሐይ የሚገኝ ኃይል፣ በኬንያ ከንፋስ የሚገኝ ኃይል፣ በውሃ የሚመነጭ ኃይል በጋና፣ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ባይደን የፀሐይ ኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት የሚውል አዲስ የ100 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክ ይፋ አድርገዋል። ይህ እየሰራንባቸው ካሉ ተነሳሽነቶች እና ፕሮጀክቶች ጥቂቶቹ ናቸው።"

ብሊንከን በመግለጫቸው ማገባደጃ እንደ ዋግነር ያሉ የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊዎች የአፍሪካ ሀገራትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚበዘብዙ እና ካሉበት ሁኔታ የበለጠ ችግር ውስጥ እንደሚከቷቸው አሳስበው፣ ሀገሮች ይህን የሚቋቋሙበት አቅም እንዲያጎለብቱ አሜሪካ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

"ዋናው ነገር ምንድነው፣ በዚህ ሳምንት በነበሩን ንግግሮች የሰማኃቸው፣ ከዚህ በፊትም በአፍሪካ ያሉ አጋሮቻችን የነገሩን የተፈጥሮ ኃብታቸው እንዲበዘበዝ እንደማይፈልጉ ነው። የህዝባቸው ሰብዓዊ መብት እንዲጣስ አይፈልጉም። መንግስታቸው እንዲዳከም አይፈልጉም። ስለዚህ ይህ ማለት ዋግነርን አይፈልጉም ማለት ነው።"


ብሊንከን መግለጫቸውን ያጠናቀቁት፣ አሜሪካ በሶስቱ ቀን ጉባዔ የገባቸውን ቃሎች ወደ ተግባር ለመለወጥ ቁርጠኛ መሆኗን በማመልከት ነው። ለዚህም በመጪው አመት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ኻሪስን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስታቸው ባለስልጣናት ወደ አፍሪካ ጉዞ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።