ኦሮምያ ውስጥ ለሚፈፀሙ ጥቃቶች መንግሥት አፋጣኝ መፍትኄ እንዲያበጅ ኢሰመኮ አሳሰበ

  • ቪኦኤ ዜና

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አርማ/ ከፌስቡክ ገፅ ላይ የተወሰደ

“በኦሮምያ ክልል በሲቪሎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ የአካል ጉዳትና መፈናቀል የፌዴራል መንግሥቱን አፋጣኝ እርምጃና ተጨባጭ ዘላቂ መፍትኄ የሚሻ ነው” ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳስቧል።

ከሐምሌ 2014 እስከ ኅዳር 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተከሰቱ ግጭቶችንና የተፈፀሙ ጥቃቶችን፣ በተጨማሪም በእነዚህ ሳቢያ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ሲከታተል መቆየቱን ኮሚሽኑ ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ክትትል ሲያደርግባቸው የቆዩ ‘ከዚህ ቀደም ግጭት የተከሰተባቸው’ ወይም ‘እየተከሰተባቸው ያሉ’ ተብለው የተመዘገቡ አካባቢዎችንም ዘርዝሮ ክትትሎቹ ምሥራቅ ወለጋን ጨምሮ በተለያዩ አሥር ዞኖች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎችን እንደሚያካትቱ አመልክቷል።

ከሐምሌ 2014 እስከ ኅዳር 2015 ዓ.ም. ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ኮሚሽኑ “ለማሰባሰብ በቻለው መረጃዎች መሠረት በታጣቂ ቡድኖቹ በተፈፀሙ ጥቃቶች በብዙ መቶዎች የሚገመቱ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን” አመልክቷል።

ብዛታቸው የማይታወቅ ሰዎች ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ደግሞ ከሚኖሩበት ቀየ መፈናቀላቸውንም ጠቅሷል።

“በተዘረዘሩት አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ እራሳቸውን እንዲከላከሉ በሚል በመንግሥት የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሌሎች ክልሎች ጭምር እንደመጡና በተለምዶ በአካባቢው የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸውን የሚነገሩ የታጠቁ ቡድኖች እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደሚንቀሳቀሱ” ኢሰመኮ አመልክቷል።

ታጣቂዎቹ ቡድኖችና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለያዩ ወቅቶች እርስ በርሳቸው እንደሚዋጉ፣ በሌላ ወቅት ደግሞ በተናጠል ጥቃቶችን እንደሚያደርሱ፣ በዚህ ምክንያትም ሳቢያ ብዙ ሲቪሎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን፣ ብዙ ንብረትም መውደሙን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው “በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ይፈፀማሉ” ያላቸውን ግድያዎችም አስመልክቶ "አንዱን ወይም ሌላኛውን “ታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ” በሚል ከፍርድ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች፣ ተገቢ የሆነ ማጣራት ሳይደረግ ታጣቂ ቡድኖችን ዒላማ በማድረግ በሲቪል ሰዎች የመኖርያ ሠፈሮች አቅራቢያ የተፈፀሙ የአየር ጥቃቶች፣ ሕገ ወጥና የዘፈቀደ እሥራቶች፣ ተጠርጠሪዎችን የማሠቃየት አድራጎቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛሉ" ብሏል።

በታጣቂ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር በዋሉ አካባቢዎች ይፈፀማሉ ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችንና አድራጎቶችን ሲያብራራ “መንግሥትን ወይም ሌላኛውን ታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ ወይም የመንግሥት ኃላፊ ናችሁ ወይም መረጃ አቀብላችኋል” በሚል የሚደርሱ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎች፣ ሌሎች ጥሰቶች፣ በግዳጅ የሚጠየቁ የገንዘብ ክፍያዎች የአካባቢዎችን ነዋሪዎችና ማኅበረሰብ ከግጭቶቹና ከጥቃቶቹ ባልተናነሰ ለሥቃይ የዳረጉ መሆናቸውን ከተጎጂዎችና ከተጎጂ ማኅበረሰብ በየጊዜው የሚደርሱት መረጃዎችና አቤቱታዎች ያሳያሉ" ብሏል የኮሚሽኑ መግለጫ።