ከአል-ሻባብ ጋር ፍልሚያው እንደሚቀጥል የሶማልያ ፕሬዚዳንት አስታወቁ

  • ቪኦኤ ዜና

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ ዛሬ ኅዳር 6/2015 ዓ.ም በትዊተር ገፃቸው ላይ ያጋሩት

ከአል-ሻባብ ጋር እየተደረገ ያለው ፍልሚያ እንደሚቀጥል የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ ለፓርላማቸው ዛሬ አሳውቀዋል። ሃገራቸው እየተጋፈጠች ስላለችው የረሃብ አደጋም ተናግረዋል።

ዛሬ፤ ማክሰኞ ለተከፈተው የሶማሊያ ፓርላማ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ በአሸባሪነት ላይ የሚደረገውና “አጠቃላይ ጦርነት” ያሉት ዘመቻ እንደሚቀጥል ዝተዋል።

“ሶማሊያ በቅርቡ በአል-ሻባብ ላይ ባደረገችው ጥቃት ድል ተቀዳጅታለች” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

“ኻዋሪጅ” ብለው ከጠሯቸው ፅንፈኛ ተዋጊዎች ጋር ለሚደረገው ትግል የአካባቢ ሚሊሽያ ታጣቂዎች ስለሰጡት ድጋፍ አድንቀዋል። ኻዋሪጅ - ከእስልምና ያፈነገጠ ሰው እንደማለት ነው።

“በዚህ ወቅት ለአገራችንንና ሕዝቧ ጠላትን መደምሰስ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። አገራችንን ከኻዋሪጆቹ ነፃ ለማውጣት ቆርጠናል።” ብለዋል።

ባለፉት ወራት ብሄራዊው ጦር ከአካባቢ ሚሊሽያ ጋር በመተባበር በማዕከላዊ ሶማልያ በርካታ መንደሮችን ከአል-ሻባብ አስለቅቋል።

አክራሪዎቹ ተዋጊዎች ሼክ ሞሃመድ ባለፈው ግንቦት ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ባለፈው ሐምሌ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው ያልተጠበቀ ጥቃት ሥንዝረዋል፤ በዚህም ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎቹ አልቀዋል። ጥቅምት ውስጥ ደግሞ በሁለት መኪኖች የተጠመደ ቦምብ ሞቃዲሹ ውስጥ አፈንድተው የ120 ሰው ሕይወት ቀጥፈዋል።

ፕሬዝደንት ሞሃመድ በዛሬው የፓርላማ ንግግራቸው ‘ታይቶ የማያውቅ’ ያሉት ድርቅ ያስከተለውና በአስከፊ ሁኔታ ያንዣበበውን የረሃብ ጉዳይም አንስተዋል። ድርቁ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እንደደቆሰም ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው፣ 15 ሚሊዮን ከሚሆኑት አጠቃላይ ሶማልያዊያን ግማሽ የሚሆኑት አስከፊ ነው የተባለ ረሃብ ከፊታቸው ተደቅኗል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዝናብ ለአምስተኛ ተከታታይ ወቅቶች ሳይጥል በመቅረቱ ኢትዮጵያ፣ ሶማልያና ኬንያ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከብቶች አልቀዋል።