በታንዛኒያ 43 ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን ሰሜናዊ ምዕራብ ቡኩባ ከተማ ሲቃረብ ተከሰከሰ። አውሮፕላኑ በመጥፎ የአየር ጸባይ ሳቢያ ቪክቶሪያ ሃይቅ ውስጥ የተከሰከሰ ሲሆን የ 3 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የታንዛኒያ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
“ፕሪሲዥን ኤር የተሰኘው አየር መንገድ አውሮፕላን ከአየር ማረፊያው በ100 ሜትሮች ርቀት በውሃ ውስጥ ተከስክሷል።” ሲሉ የክልሉ ፖሊስ አዛዥ ዊሊያም ምዋምፓጋሌ በአየር ማረፊያ ውስጥ በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
39 ተጓዦችን፣ ሁለት አብራሪዎችን እና ሁለት የበረራ አስተናጋጆችን በድምሩ 43 ሰዎችን ይዞ ከታንዛኒያ ዋና ከተማ በበረራ ቁጥር PW 494 የተነሳው የንግድ አውሮፕላን በሃይቁ ዳርቻ ወዳለ ካገራ ወደ ተሰኘ ክልል እየተጓዘ እንደነበር የክልሉ ኮሚሽነር አልበርት ቻላሚላ አስታውቀዋል።
ቻላሚላ አክለውም “አሁን እየተነጋገርበት ባለው ሰዓት 26 ሰዎችን ከሃይቁ ማውጣት የቻልን ሲሆን ወደ ሪፈራል ሆስፒታል ልከናቸዋል” ብለዋል። “የነፍስ አድን ስራው አሁን የቀጠለ ሲሆን ከአብራሪዎቹ ጋር እየተነጋገርን ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ አውሮፕላኑ ATR-42 የተሰኘ በጣሊያን ቱሉዝ በሚገኝ የፈረንሳይ እና የጣሊያን ኩባኒያ የተመረተ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የታንዛኒያ ትልቁ የግል አየር መንገድ የሆነው ፕሪሲዥን ኤር ኩባኒያው የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ወደ አደጋው ሥፍራ መላኩን አስታውቋል።
“ፕሪሲዥን ኤር አየር መንገድ የቴክኒክ ሰራተኞች እና የታንዛኒያ ኤርፖርት ባለስልጣናትን ያቀፈ የምርመራ ቡድን አሁን በስራ ላይ ያለውን የነፍስ አድን ቡድን ለመቀላቀል ተነስቷል” ሲል ኩባኒያው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የታንዛኒያ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም ግማሽ አካሉ ከሰመጠው አውሮፕላን ሰዎችን ለማትረፍ ዓሳ አጥማጆችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እርዳታ ለመስጠት በውሃ ውስጥ ሲዘዋወሩ የሚያሳዩ የቪድዮ ምስሎችን አጋርተዋል።
የሃገሪቱ ፕሬዘዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን በአደጋው ለተጎዱት ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ፕሬዘዳንቷ “የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቹ ስራቸውን እየሰሩ እንዳሉ እኛ ተረጋግተን እግዚአብሔር እንዲረዳን እንጸልያለን” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።