በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚደርሱ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት በረጅም ርቀት እና አገር አቋራጭ የጭነት ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች የሚደርሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን አሽከርካሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። በዚህ አመት ብቻ እስከ አርባ የሚደርሱ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ህይወት ማለፉን የሚገልፁት አሽከርካሪዎች፣ በየጊዜው በሚፈፀሙ እገታዎችም ቤተሰቦቻቸው ከ150 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር እንዲከፍሉ የሚጠየቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሱ የደህንነት ችግሮች መረጃ እንደደረሰው ያስታወቀው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር በበኩሉ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ዘረፋና ግድያዎቹን ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ለኢትዮጵያ የገቢ ወጪ እንቅስቃሴ ትልቅ ድርሻ የሚወስዱት የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች፣ በየግዜው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ በሚሄደው የፀጥታ ችግር ምክንያት ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ይገልፃሉ። በመንገድ ላይ በሚያጋጥሙ መንገድ መዘጋት፣ አሽከርካሪዎችን ማስቆም፣ ገንዘብ መጠየቅ፣ ንብረት መዝረፍ፣ አሽከርካሪዎችን አግቶ ገንዘብ መጠይቅ እና ተኩሶ በመግደል በመሳሰሉ ችግሮች ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሶ ማሽከርከር የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩም የአሽከርካሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ገቢ እና ስነ-ልቦና በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱን ያስረዳሉ።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋሁን ከበደ ኪዳኔ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ሲሆኑ ለ16 አመት በተሳቢና ገልባጭ መኪና አሽከርካሪነት አገልግለዋል። በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በሚሰሩበት የመተኻራ እና አዋሽ መንገድ የሚገጥማቸው ተደጋጋሚ ዝርፊያ ምክንያት ግን ደህንነታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ይናገራሉ።
ሌላው ያነጋገርናቸው አቶ ሰጡ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ እና የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ የከተማው ድምበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማህበርም አባል ናቸው። ለ13 አመታት ያሽከረከሩበት የሱዳን መንገድ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሚፈፀምበት የዝርፊያ፣ የግድያ እና የእገታ ወንጀል ምክንያት ግን ስራቸውን እንደቀድሞው መስራት አለመቻላቸውን ይገልፃሉ። በተለይ ደግሞ "ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተባባሰ ነው" ባሉት የአሽከርካሪዎች እገታ፣ ወንጀለኞቹ ከ150 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር እንደሚጠይቁ ያስረዳሉ።
አቶ ሰጡ አክለው በዚህ አመት ብቻ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ አሽከርካሪዎች በጥይት ትመተው ህይወታቸው ማለፉን ገልፀዋል።
አቶ አበባው ጋሽውም እንዲሁ በጅቡቲ መስመር አገር ቋራጭ ሹፌር ሆነው ለ23 አመታት ያገለገሉ ስሆን ከሶስት ወር በፊት አፋር ክልል ገዋኔ ላይ ያጋጠማቸውን ዝርፊያ እንዲህ ይገልፁታል።
ይህ ሁሉ ወንጀል ሲፈፀም የፀጥታ አካላት ርምጃ አልወሰዱም ወይ ብለን ላቀረብነው ጥያቄ አቶ አበባው መልስ አላቸው
አቶ ተስፋሁን በበኩላቸው የፀጥታ አካላት እንደውም መፍትሄ ከመሆን ይልቅ የችግሩ አካል ሆነዋል ይላሉ።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚደርሰው ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት በአሽከርካሪዎች እንደልብ ተንቀሳቀሰው ማሽከርከር ባለመቻላቸው በቤተሰባቸው ላይ እያደረሰ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና አቶ ሰጡ በምሬት ያስረዳሉ።
አቶ ሰጡ አክለው የፀጥታ አካላት እና የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸው ለጥቃቶቹ መባባስ እና መጠናከር አስተዋፅኦ አድርገዋል ሲሉ ይከሳሉ።
በዚህ ጉዳይ ያናገርናቸው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ ታጠቅ ነጋሽ፣ መስሪያ ቤታቸው በአሽከርካሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር መገንዘቡን እና ችግሩን ከፌደራል እና የክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት ከሁለት ወራት በፊት ጥረት መጀመሩን ገልፀው ትኩረት አልሰጠም መባሉ ትክክል አለመሆኑን ይገልፃሉ።
የፀጥታ አባላት ያደርሱታል የተባለውን የዝርፊያ ችግር በተለመለከተ የፀጥታ መዋቅሩ ርምጃ እንደሚወሰድ ያሰመሩበት አቶ ታጠቅ በተለይ ከፍተኛ ዝርፊያ እና ግድያ እንደሚፈፀም መረጃ በደረሳቸው የአፋር ክልል ችግሩን ለመቅረፍ እየተደረገ ባለው ጥረት መሻሻሎች መኖራቸውን አስረድተዋል።
ለሀገሪቱ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ንግድ የአጀርባ አጥነት ሆነው የሚያገለግሉት የረጅም ርቀት እና ድምበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ግን በህይወታቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ የተደቀነው አደጋ ከመንግስት ከፍተኛ አትኩሮት እና ርምጃ የሚፈልግ መሆኑን በመግለፅ ለደህንነታቸው ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።