የተመድ ዋና ጸሀፊ የሱዳን ብሉ ናይል ግጭት እንዳሳሰባቸው ገለጹ 

  • ቪኦኤ ዜና

የተምድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ (ፎቶ ፋይል)

በሱዳን ብሉ ናይል ክፍለ አገር፣ ዋድ ኤል ማሂ እና ደማዚን በተባሉ ከተሞች በቅርብ ቀናት የተባባሱ ግጭቶች የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽን በእጅጉ ያሳሰባቸው መሆኑን ቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱጃሪክ ትናንት ባወጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡

ዋና ጸሀፊው ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቁ ሲሆን በግጭቱ ለሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች መጽናናት እና የቆሰሉትም ፈጥነው እንዲያገግሙ መመኘታቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

የሱዳን ባለሥልጣናት በግጭቱ እና በማህበረሰቦች መካከል ባሉት ሌሎች ግጭቶችና ጥቃቶች ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ በማድረግ፣ የድርጊቱ ተሳታፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ዋና ጸሀፊው መጠየቃቸውንም ቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱጃሪክ አስታውቀዋል፡፡