ህወሓት ወደ ሰላም ሂደቱ ለመግባት ፈቃደኝነቱን ገለጸ

ፎቶ ፋይል - በደብረታቦር፣ ኢትዮጵያ፣ እእአ 12/6/2021

ከኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ ያለው ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)፣ “ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚደረገው የሰላም ሂደት ተሳታፊ ለመሆን” ፈቃደኛ እንደሆነ ማስታወቁን የቪኦኤው ፍረድ ሃርተር ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

ህውሃት አክሎም “ወዲያውኑ ተፈጻሚ ለሚሆን” የተኩስ አቁምና ያንን ተከትሎም በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት ለሚደረግ የሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት አሁን ወደ ሁለተኛ ዓመቱ እየተቃረበ ሲሆን በአስር ሺህዎች የሚገመቱ ሰዎች መገደላቸውንና በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ ካለ መሰረታዊ አቅርቦቶች አስቀርቷል።

ትናንት እሁድ ማምሻውን የወጣው የህወሃት መግለጫ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ጦርነቱ አገረሽቶ ለወራት የነበረውን አንጻራዊ መረጋጋት ካደፈረሰ በኋላ አሜሪካና ሌሎች ወገኖች ግፊት ማድረጋችውን ተከትሉ የወጣ ነው ብሏል ሪፖርቱ።

ለጦርነቱ እንደገና መጀመር አንዱ ወገን በሌላኛው ያመካኛል።

ህወሃት ከዚህ ቀደም በኦሊሲጉን ኦባሳንጆ መሪነት በአፍሪካ ህብረት ይደረግ የነበረውን የሰላም ጥረት ሲነቅፍና እንደማይቀበለውም ሲያስታውቅ የቆየ ሲሆን፣ አዲስ ያወጣው መግለጫ “ሁለቱም ወገኖች የሚቀበሏቸውን ሸምጋዮች” እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችና ባለሙያዎች ሂደቱን የሚመሩበት እንዲካሄድ እንደሚኖር ህወሃት የሚጠብቅ መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል። ከዚህ በፊት ህወሃት ድርድሩ በኬንያው መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ሸምጋይነትና በአሜሪካ ታዛቢነት ናይሮቢ ውስጥ እንዲካሄድ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቶ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚሰጥቸው መግለጫዎች ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታና በየትኛውም ስፍራ ንግግር ለማድረግ ፍላጎቱን ሲያሳይ ቢቆይም የህወሃት ወገን ደግሞ በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እንዲሁም የኤርትራ ሃይሎች ከትግራይ ይውጡ ሲል እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ነበር።

አሜሪካ፣ የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህወሃትን ጥሪ በመልካም ተቀብለዋል። በተጨማሪም አሜሪካ፤ ኤርትራ እና “ሌሎች” ያለቻቸውን በስም ያልተጠቀሱ አካላት ጦርነቱ ላይ ነዳጅ ከማርከፍከፍ ይቆጠቡ ብላለች።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር “በኢትዮጵያ ሰላምን ለመመልስ ልዩ አጋጣሚ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

የኢትዮጵያ መንግስት የህወሃትን መግለጫ በተመለከተ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ ምላሽ ባይሰጥም ከዚህ በፊት በሰጣቸው መግለጫዎች ግን ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታና በየትኛውም ስፍራ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል።