የጦርነቱ ስድስተኛ ቀን ወሬ

Your browser doesn’t support HTML5

በአማራና በአፋር ክልሎች የግንባር አካባቢዎች ቁጥሩን አረጋግጦ ለመናገር የማይቻል ብዛት ያለው ሰው እየተፈናቀለ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ማምሻውን ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ደባርቅ፣ ደሴና ወልድያ ላይ ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት የሰዓት እላፊ ገደብ በመጣሉ በሲቪሎች እንቅስቃሴ ላይ ጫና ማሳደሩን፣ የህክምናና የንግድ አገልግሎቶችን ለማግኘትም እክል መፍጠሩን ቃል አቀባዩ አክለው ጠቁመዋል።

ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ በየብስ ማድረስ ካለፈው ረቡዕ፤ ነኀሴ 18 አንስቶ የተቋረጠ መሆኑንና ከማግስቱ ነኀሴ 19 አንስቶ ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች የአየር አገልግሎት ወደ መቀሌ ለመብረር አለመቻሉን፣ በዚህም ጥሬ ገንዘብ ማድረስና ተለዋዋጭ ሠራተኞችን ማሠማራት አዳጋች እንደሆነበት ዱጃሪክ ተናግረው ድርጅቱ የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታው በፈቀደ መጠን መንግሥታዊ ካልሆኑ አጋሮች ጋር በመተጋገዝ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ለማድረስ መጣሩን እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ትግራይ ውስጥ ሰብዓዊ አጋሮች ምግብና ሌሎችም አስፈላጊ አቅርቦቶችን ማከፋፈል እንደገና መጀመራቸውን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

ዛሬም ለስደስተኛ ቀን ቀጥሎ በዋለው የሰሜን ጦርነት “ህፃናት እንዳይጎዱ በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት ግዳጄን እየተወጣሁ ነው” ሲል ፌዴራል የመከላከያ ሠራዊት አስታውቋል። የህወሃት ኃይሎች “ህፃናትንና ሴቶችን ከፊት አሰልፈው እየተዋጉ ናቸው” ሲል ከሷል።

የህወሓት መሪዎች ህፃናትን ወደ ጦር ግንባር ማሠማራትን አስመልክቶ ከዚህ ቀደምም ይቀርቡባቸው የነበሩ መሰል ውንጀላዎችን በተደጋጋሚ ሲያስተባብሉ የቆዩ ሲሆን አዲስ በቀረበባቸው ክስ ላይ እስካሁን በይፋ የተሰማ ምላሽ የለም።

ለጦርነቱ መጀመር አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ በሚያደርጉበት ጦርነቱ ተባብሶ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ተኩስ በአፋጣኝ እንዲቆም ከሃገር ውስጥና ከውጭ የሚሰሙ ተማፅኖዎችም ቀጥለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ በዛሬ የተስያት መግለጫቸው ላይም ተዋጊዎቹ ወገኖች በዓለምአቀፍ የሰብዓዊነት ህግ መሠረት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደገና ለማስጀመር ለረድዔት ሠራተኞች በአፋጣኝ መተላለፊያ መሥመር እንዲከፍቱ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ግጭቱን እንዲያቆሙና ውይይት እንዲጀምሩ ያሳሰበ ሲሆን በቀደሙት ጦርነቶች ወቅት ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው ዓለምአቀፍ ኮሚሽንም መሰል መልዕክት አስተላልፏል።

በሌላ በኩል ለሥራ ጉብኝት ወደ አልጄሪያ መሄዳቸው የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ጦርነቱ ካገረሸ ወዲህ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።

/ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ።/