ቡርጂ ውስጥ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ሰዎች ተገደሉ

Your browser doesn’t support HTML5

ደቡብ ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ የታጠቁ ቡድኖች አደረሱት በተባለ ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን እና አምስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ነዋሪዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች ገለፁ።

የወረዳው መንግሥት ኮምኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረወልድ ሂዶ ከተገደሉ እና ከቆሰሉ አርሶ አደሮች በተጨማሪ ከ50 በላይ ከብቶች መዘረፋቸውን አስታውቀዋል። በጥቃቱም ሱሮ ባርጉዳ መሽገዋል ያሏቸውን ታጣቂ ቡድን ወንጀለዋል።

በተመሳሳይ ታጣቂ ቡድን በአማሮ ወረዳ በተፈፀመ ጥቃት አንድ አርሶ አደር መገደሉን የአማሮ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ይንቀሳቀስባቸዋል ከተባለው ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወይም ሠራዊት ቃል አቀባይ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ኦዳ ተርቢ ከዚህ ቀደም በዚህ አካባቢ ስለሚደርሰው ጥቃት ተጠይቀው ውንጀላውን ማስተባበላቸው ይታወሳል።