ናይጄሪያ የቻይና ዜግነት ያላቸውና ሌሎች የተጠለፉ ዜጎቿን አሰሳ ላይ ነች

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፡ በእሁድ አምልኮ ላይ እያለች በታጣቂዎች የተገደለችው የ51 ዓመቷ ትሬዛ ኦግቡ ቤተሰብ ኦ ኦንዱ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ለሮይተርስ ቃለ ምልልስ በሰጡበት ወቅት። / ጁን 7, 2022.

የታጠቁ ሰዎች ማዕከላዊ ኒጄር በምትሰኘው የናይጄሪያ ግዛት የሚገኝን የማዕድን ማውጫ አጥቅተው አራት የቻይና ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ጠልፈው ከወሰዱ በኋላ የሀገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ጠላፊዎቹን ፍለጋ ላይ ናቸው።

ረቡዕ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የማዕድን ማውጫው ሠራተኞች መገደላቸውን የሀገሪቱ ሚዲያዎች በመዘገብ ላይ ናቸው።

ጸጥታ በራቃት ናይጄሪያ የቻይና ዜግነት ያላቸው የማዕድን ሠራተኞች ሲጠለፉ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ግዜ ነው።

የአጃታ አቦኪ ማዕድን ማውጫው ወደሚገኝበት ሽሮሮ ወደ ተባለ ስፍራ ተጨማሪ ኃይል እንደተላከ የሃገሪቱ የፖሊስ ኮሚሽነር መንዴይ ባላ-ኩርያስ ተናግረዋል።

ባላ-ኩርያስ አክለውም የማዕድን ማውጫው የሚገኘው ራቅ ወዳለ ጫካ ቢሆንም የድረሱልኝ ጥሪ እንደተሰማ የተወሰኑ የፀጥታ ኃይላት ወዳያውኑ አጥቂዎቹን አሳደዋል ብለዋል።

በጥቃቱ አራት የፖሊስ አባላት እንደተገደሉና የጸጥታ ኃይሎችም የተወሰኑ ታጣቂዎችን መግደላቸውን ለቪኦኤ የገለጹት ኮሚሽነሩ ምን ያህል ብዛት ያላቸው የጸጥታ ኃይሎችና እነርሱን ሊረዱ የገቡ በጎ ፈቃደኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በናይጄሪያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ እስከ አሁን በጉዳቱ ላይ መግለጫ አሰልጠም። ቪ ኦ ኤ ኤምባሲውን ለማነጋገር ሞክሮም አልተሳካም።

የግዛቲቱ ሃገረ-ገዢ አቡባከር ሳኒ-ቤሎ ጥቃቱን “ዘግናኝ” ሲሉ ጠርተው የጸጥታ ሃይሎች በግዛቲቱ ሰላም እንዲመለስ እያደርጉ ካለው ጥረት እንዳይዘናጉ አሳስበዋል።

ፓትሪክ አግባምቡ የተባሉ በአቡጃ የሚኖሩ የጸጥታ ጉዳዮች ባለሞያ በግዛቲቱ ከሚታዩ ጥቃቶች መበርከት አንጻር የጸጥታ ኃይሎች ይበልጥ ንቁ መሆን እንደነበረባቸው ተናግረዋል።

“ኒጄር ግዛት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ጥቃት በቅርቡ በተደጋጋሚ ታይቷል። ስለዚህ ተጨማሪ ጥበቃ እንዲኖር ያስፈልጋል። ገንዘብም ሆነ ትኩረትን ለማግኘት የውጪ ዜጎችን ተመራጭ ኢላማ ናቸው። ይህ ድርጊት እየጨመረ ከሄደ ናይጄሪያ ለንግድ አስቸጋሪ ሃገር ልትሆን ትችላለች” ብለዋል የጸጥታ ባለሞያው።

በናይጄሪያ በርካታ ግዛቶች ጥቃቶች እየጨመሩ መጥተዋል። ተንታኞች እንደሚሉት ወንጀለኛ ቡድኖች ከቀጣሪዎቻቸው ረብጣ ገንዘብ ለማግኘት የውጪ ዜጎችን ያፍናሉ። ባለፈው ጥር ሽሮሮ በሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚሠሩ ሦስት የቻይና ዜጎች ታግተው ነበር።

ቤጂንግ በናይጄሪያ የሚሠሩ ዜጎቿ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ስታሳስብ ቆይታለች። ባለፈው ግንቦትም የቻይና ባለስልጣናትና በናይጄሪያ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች ወኪሎች በጸጥታ ጉዳይ ምክከር አድርገው ነበር።

/ዘገባው የቲመቲ ኦቢይዙ ነው እንግዱ ወልዴ ወደ አማርኛ መልሶታል/