በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው የበዛ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ከጥቃቱ አመለጥን ያሉ የዐይን እማኞች እና የሟቾቹ ቤተሰቦች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ጥቃቱ የደረሰባቸው “አማራ” በመሆናቸው ብቻ መሆኑን ገልፀው በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር የተለያየ መሆኑን ይናገራሉ። ማምሻውን በዚህ ጉዳይ ላይ ዘገባ ያወጣው ሮይተር የዜና ወኪል ነዋሪዎቹ ጠቅሶ የሟቾች ቁጥር 260 መሆኑን አስነብቧል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ሸኔ መሆኑን የገለፁት የጊምቢ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሻፌ ዓለሙ ሕጻናትን እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
ድርጊቱን ያወገዙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ "ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላምና ደህንነት መመለስ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው ብለዋል።
የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥትም በጥቃቱ ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሠማውን ሐዘን ገልጿል ።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውና መንግሥት ሸኔ በማለት በአሸባሪነት የፈረጀው ሸማቂ ቡድን “ግድያውን አልፈጸምኩም” ብሏል።
የድርጅቱ ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ኦዳ ተርቢ “ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ የከፈቱት የመንግሥት ኃይሎች ናቸው" ሲሉ አስተባብለዋል።
Your browser doesn’t support HTML5
/ሙሉ ዘገባውን ከተያይዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ/