የኢትዮጵያ መንግሥት "ሰላም ለማምጣት እየሠራሁ ነው" አለ

Your browser doesn’t support HTML5

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማምጣት እየሠረሁ ነው አለ

የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እና ግጭት በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ሰላምን ለማውረድ ስለሚከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

በህወሓት በኩል ያሉ እንቅስቃሴዎች ግን ስጋት እየፈጠሩባቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ህወሓት ወይም ትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው መንግሥት በበኩሉ ትግራይን በመክበብ እና ሰላም እንዳይመጣ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ ሲከስ መቆየቱ ይታወሳል።

ከአምባሳደር ዲና መግለጫ በኋላ፣ በአፍሪካ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው አዲስ የተሾሙት ማይክል ሀመር ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች በሚደረገው የሰብዓዊ አቅርቦት፣ በግጭቱ ወቅት ለተፈፀሙ በደሎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተወሰዱ እርምጃዎች እና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በሚካሄደው የሰላም ጥረት እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሌላ ዜና፣ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ያላትን ድርሻ ስለማጣቷ የወጡ መረጃዎችን በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና፣ መረጃው በመጣራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡