በኢትዮጵያ በተለያዩ ዲጂታል ሚዲያ ላይ የሚሠሩ ከአሥር በላይ አዘጋጆች ከትላንት በስቲያ ትናንት እና ዛሬ መታሰራቸውን ቤተሰቦቻቸው ገለፁ።
Your browser doesn’t support HTML5
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን በቀጥታ ያለው ነገር ባይኖርም ትላንት ባወጣው ከእስር ጋር የተያያዘ መግለጫ በሁሉም ክልሎች በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እየዋለ መሆኑን ገልፆ ነበር።
በተለያዩ መጽሄቶችና ጋዜጦች ላይ በፀሐፊነትና በማኅበረሰብ አንቂነት የምትታወቀው በሙያዋ መምህር የሆነችው መስከረም አበራ ዛሬ ከባሕርዳር ወደ አዲስ አበባ ስትመለስ ቦሌ አይሮፕላን ጣቢያ ላይ መያዟና እስካሁን የት እንዳለች እንደማይታወቅ ባለቤቷ አቶ ፍፁም ገ/ሚካኤል ገልጿል።
ከረጅም ዓመታት በፊት “ሻይ ቡና” በተሰኘ የቴሌቭዥን ፕሮግራም የሚታወቀውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ “ገበያኑ በተሰኘ” የዩትዩብ ቻናል ላይ ሐሳቡን የሚያቀርበው ሰሎሞን ሹምዬ መያዙንም የቅርብ እህቱና ጠበቃው ተናግረዋል።
ሰሎሞን ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረቡንና የቀረበበት ውንጀላም “በሚድያ ሁከት የሚያስነሳ መግለጫ ሰጥቷል” የሚል መሆኑን ጠበቃው አቶ በፍቃዱ ስዩም ተናግረዋል።
በተጨማሪም “ንስር” እና “አሻራ” የሚባሉ የዲጂታል ሚዲያ ውጤቶች ስምንት አዘጋጆች ከትላንት በስተያ ባህር ዳር ከተማ በሚገኘው ቢሮአቸው ውስጥ ሥራ ላይ እንዳሉ መያዛቸውን አሻራ ሚድያ ላይ የሚሠራው የጋሻዬ ፈረደ ባለቤት ወ/ሮ ብሌን ተጫነ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
አዘጋጆቹ ትላንት ለሊት ወደ ንፋስ መውጫ ማረሚያ ቤት እንደተወሰዱ ፊት ለፊት በርቀት ከመተያየት ውጭ መገናኘት እንደማይቻልና በሰው በኩል እቃ እንደላኩላቸው ተናግረዋል
በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ስልክ ላይ ከትላንት ጀምሮ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ስልካቸው ስለማይነሳ ልናገኛቸው አልቻልንም። ከሌላ የኮምዩኒኬሽንስ ቢሮ ኃላፊ ባገኘነው መረጃ አብዛኛው የመንግሥት ባለሥልጣናት ስብሰባ ላይ መሆናቸው ተነግሮናል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት እየተካሄደ ባለው በዚህ የማሠር እንቅስቃሴ ላይ እስካሁን በቀጥታ ያለው ነገር የለም። ይሁን እንጂ መንግሥቱ ትላንት ባወጣው መግለጫ “በተለይ የጋዜጠኝነትን ካባ በመልበስ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መንግሥት የሚወሰደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ዝርፊያ፣ ስርዓት አልበኝነትና ውንብድና በመበራከቱ የሕዝቡን ቅሬታ መሠረት በማድረግ በሁሉም ክልሎች በወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን መንግሥት በቁጥጥር ሥር እየዋለ መሆኑን በዚሁ መግለጫው ገልጿል።