ዚምባብዌ መንግስቱ ኃይለማሪያምን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፍቃደኛ እንደሆነች አሳወቀች

  • ቪኦኤ ዜና

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም/ ፎቶ ፋይል/ኤፒ

በዘር ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱትን የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃይለማሪያምን ወደ ሃገራችው ለመመለስ ሃራሬ ፍቃደኛቷንና ከቀድሞው በበለጠ ግልጽ የሚያድርግ አቋሟን በውጪ ጉዳይ ምኒስትሯ በኩል አስታውቃለች።

የሃገሪቱ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ፍሬደሪክ ሻቫ ከአሜሪካ ድምጽ የዚምባቡዌ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የቀድሞው ፕሬዝደንትን በተመለከተ ለዚምባቡዌ መንግስት ህጋዊ ጥያቄ የሚያቀርብ ከሆነ መንግስታቸው እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ምኒስትሩ መግለጫ ከዚህ በፊት እ.አ.አ የቀን አቆጣጠር በ 2009 ዓ.ም የቀድሞው የሃገሪቱ የማስታወቂያ ምኒስትር ቲቻዎና ጆኮንያ ለአሜሪካ ድምጽ ከተናገሩትና ሃገራችው የቀድሞው ፕሬዝደንቱን ወደ ኢትዮጵያ እንደማትምልስ ከገልጹበት አቋም የተለየ ነው።

“መንግስቱ ዚምባቡዌ የመጣው አምልጦ ነው። እንደ ስደተኛ ነው የገባው። በተመድ ህግ መሰረት ደግሞ ስደተኛ በሚሄድበት ሀገር ከለላ ያገኛል።” ብለው ነበር የማስታወቂያ ምኒስትሩ።

ኮሎኔል መንግስቱ በ 1991 ሃገራችውን ጥለው ወደ ዚምባብዌ ከሸሹ በኋላ በ2008 ዓ.ም በዘር ማጥፋት፣ በግድያ፣ ከህግ ውጪ ሰዎችን በማሰርና ንብረትን በመውረስ ጥፋተኛ ተብለው በሌሉበት የሞት ፍርድ ተወስኖባቸዋል።

“እኛ መንግስቱን አልደበቅንም። ከሀገሩ ሕዝብ ጋር ችግር ውስጥ ሲገባ ዚምባብዌ በመምጣቱ እንዲከርም ፈቅደንለታል።” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ምኒስትሩ።

በተያያዘ ዜና የውጪ ጉዳይ ምኒስትሩ እንዳሉት በ1994 ሩዋንዳ ውስጥ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ተጠያቂ የነበረውና በኋላም በ2006 እዛው ዚምባብዌ በ50 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው ፕሮታይስ ፒራንያ እንዴት ወደ ሃገሪቱ እንደገባና ሳይታውቅ ተደብቆ እንደኖረ ለማወቅ በተመድ እየተካሄደ ላለው ምርመራ መንግስታችው ተባባሪ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

በዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ጥፋተኛ የተባሉትና የፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ አዛዥ የነበሩት ፒራንያ ዝምባብዌ መኖራቸው የታወቀው ሞተው ከተገኙ በኋላ መሆኑንንና ሃገራቸው ግለሰቡን ደብቃ አቆይታለች የሚለውን ክስ እንደማይቀበሉ ምኒስትሩ ጨምረው አስታውቀዋል።