በመቀሌ ከተማና አቅራቢያው ተፈፀመ በተባለ የአየር ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

አይደር ሆስፒታል

  • የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊቱን አስተባብሏል

በመቀሌ ከተማና በአቅራቢያው ባለ ገጠር ቀበሌ ተፈጽሟል ባሉት የአውሮፕላን ጥቃት የሰው ሕይወት ማለፉና ነዋሪዎች መቁሰላቸውን፤ በጥቃቱ የተጎዳ ነዋሪና የሕክምና ባለሞያ ገለፁ።

ዛሬ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት በእንደርታ ወረዳ መሶበ ቀበሌ እንዲሁም በመቀሌ ከተማ በአዲ ሃቂ ገበያ አካባቢ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ጥቃት መድረሱን እማኞቹ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የተባለው ጥቃት ማስተባበላቸውን እና “የኢትዮጵያ መንግስት የገዛ ከተማዎን ለምን ያጠቃል? መቀሌ የኢትዮጵያ ከተማ ናት ። ’’ ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

“ንጹሃን የሚኖሩባቸውን ከተሞች ያጠቁት ሸብርተኞች እንጂ መንግሥት አይደለም ” ያሉት አቶ ለገሰ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ኃይሎችን በአጎራባቹ አፋር ክልል ውስጥ በውጊያ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ሲሉ ከሰዋል።

(ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ከድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

Your browser doesn’t support HTML5

በመቀሌ ከተማና አቅራቢያው ተፈፀመ በተባለ የአየር ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ


በተያያዘም መቀሌ አካባቢ ተፈፅሟል የተባለውን የአየር ድብደባ ወሬ እያጣራ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ጥቃት የተፈፀመባቸው አካባቢዎች “የመኖሪያ አካባቢዎች ናቸው” መባሉ “በሲቪሎች ላይ ሊደርስ ይችላል” በሚል የበረታ ሥጋት ያደረባቸው መሆኑን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱያሪች ዛሬ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“ዛሬ መቀሌ ላይ ተፈፀመ እንደተባለው የአየር ድብደባ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭቱ መስፋፋት ዋና ጸሐፊውን በጥልቅ አሳስቧቸዋል” ብለዋል ዱያሪች።

ሁሉም ወገኖች ሲቪሎችንና ሲቪል ተቋማትን ዒላማ ከማድረግ እንዲቆጠቡም ዋና ፀሃፊው ማሳሰባቸውንና ሁሉም ወገኖች ፀብ አቁመው ለህዝቡ ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ፤ የነዳጅና የመድኃኒትን አቅርቦት ጨምሮ እጅግ አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል።