ልጆችዎ ትምህርት ቤት መሄድ ቢጠሉ ምን ያደርጋሉ?

Your browser doesn’t support HTML5

ህፃናት የትምህርት መማሪያ ጊዜያቸው ደርሶ ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡ ወይም ካደጉ በኃላ በህይወታቸው በሚደርሱ የተለያዩ ገጠመኞች ምክንያት ትምህርት ቤት መሄድን ሊፈሩና ሊጠሉ ይችላሉ። በተለይ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ትምህርት ቤት ውስጥ ሊያጋጥማቸው የሚችል ዝቅተኛ የመሆን ስሜት፣ የአካባቢ መቀየር፣ በወላጅ መሀል የሚደርስ ፍቺ ወይም ሞት ልጆች ትምህርት ቤት መሄድን እንዲጠሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይህ ሁኔታ ሲያጋጥም ልጆች ፍርሀታቸውን ማሸነፍ እንዲችሉ ምን ማድረግ ይቻላል?

ፍቅረ ሰላም ጌትነት የስምንት አመት እና የአምስት አመት ልጆች እናት ናት። አሁን በትምህርታቸው ጎበዝና ታታሪ የሆኑትልጆቿ ታዲያ ትምህርት ሲጀምሩ ትምህርት ቤት ላለመሄድ በጣም ያስቸግሯት እንደነበር ታስታውሳለች። በተለይየመጀመሪያ ልጇ።

የመጀመሪያ ልጇን ያክል አይሁን እንጂ ሁለተኛ ልጇም በተመሳሳይ ትምህርት ቤት ላለመሄድ ጥረት ታደርግ እንደነበርፍቅረ ሰላም ትናገራለች። በአብዛኛው ይህን ጥላቻቸውን የሚገልፁትም በማልቀስና ትምህርት ቤት ላለመሄድ የተለያዩሰበቦችን በመፍጠር ነበር።

በዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ግዛት የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ እንዲሁም በዚሁ ዙሪያ ፀሀፊና አሰልጣኝ የሆኑት ዶክተር ሙላቱ በላይነህ እንደሚያስረዱት ይህ አይነቱ በህፃንነት እድሜ ላይ ትምህርት ቤት የመሄድ ፍራቻ ወይም ጥላቻ የሚከሰተው በእንግሊዘኛው ሰፓሬሽን አንዛይቲ ተብሎ በሚጠራው መለየት የሚፈጥረው ጭንቀት ምክንያት ነው።

ትምህርት ቤት የመሄድ ጥላቻ ወይም ፍራቻ በህፃናት ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የእድሜ ክልል ላይ ባሉ ልጆች ላይ ሊደርስ ይችላል። ለዚህ ምክንያቱ እንደየእድሜያቸው እና የአኗኗራቸው ሁኔታ እንደሚለያይ ዶክተር ሙላቱ ያስረዳሉ።

ሌላው ለልጆች ትምህርት ቤት መጥላት ምክንያት የሚሆነው ደግሞ በቤተሰብ መሃል የሚደርስ ግጭት ወይምበትምህርት ቤት ውስጥ የሚያጋጥም የዝቅተኛነት ስሜት በስነልቦናቸው ላይ የሚያሳድሮ ተፅእኖ እንደሆነ ዶክተር ሙላቱጨምረው ያብራራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት ድረጃ ዝቅተኛ መሆንና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር አብሮ መሄድ አለመቻልም እንዲሁ ለትምህርት ቤት ጥላቻ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በተለይ ወላጆቻቸው ለስራ ወይም ለኑሮ የሚኖሩበትን ቦታ ወይም ሀገር ቀይረው ወደ አዲስ ቦታ ሲሄዱ ይህ አይነቱ ችግር ጎልቶ ሊታይ ይችላል።

ልጆቻቸው ትምህርት ቤት መሄድ የሚያቸግሯቸው ብዙ ወላጆች በቁጣና በቅጣት ልጆችን ወደ ትምርህት ቤት እንዲሄዱለማድረግ ይሞክራሉ። ይህ አይነቱ አካሄድ ግን በተቃራኒው ልጆች እንዲርቁና ሌላ መደበቂያ እንዲፈልጉእንደሚያደርጋቸው የሚያስረዱት ዶክተር ሙላቱ መፍትሄው ለልጆች ግዜ መስጠትና መነጋገር መሆኑን ያሰምሩበታል።

ዶክተር ሙላቱ አክለው ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በትምህርት ቤት እንደመሆኑ መጠን ከትምህርትቤታቸውና ከመምህራኖቻቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት መፍጠርም ልጆችን ለመረዳትና ለማገዝ ቁልፍ መሰረት ነው ይላሉ።

ፍቅረሰላምም ልጆቿ ትምህርት ቤታቸውን እንዲለምዱ እና እንዲወዱ ማድረግ የቻለችው፣ በየቀኑየሚያስጨንቃቸውንና የሚረብሻቸውን እንዲያካፍሉ በግልፅ በማናገርና ከትምህርት ቤታቸውና ከመምህራኖቻቸው ጋርበመነጋገር ነበር። ይህን በማድረጓ ልጆቿ ዛሬ ትምህርት ቤታቸውን ከመውደዳቸው በላይ ከጓደኞቻቸው ተግባቢናውጤታማ መሆን ችለዋል።