የአሜሪካ መንግስትን ኢትዮጵያን የሚመለከት ወቅታዊ አቋም ያወገዘ ሰልፍ ተካሄደ

.

በዋሺንግተን ዲሲ አቆጣጠር ትናንት ማለዳ ጀምሮ ነበር የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰንደቅ ዓላማዎችን የያዙ፣ የተለያዩ መፈክሮችን ያነገቡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ደጃፍ ላይ መሰብሰብ የጀመሩት።

ቪኦኤ ያናገራቸው ተሳታፊዎች እንደገለጹልን የሰልፉ ዋና ዓላማ ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን በተመለከተ የያዘችውን ወቅታዊ አቋም የተሳሳተ መሆኑን መጠቆም፣ መቃወምም ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ውስጥ የተሳካ የህግ ማስከበር በሰራ ማግስት ፣በሀሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የሀገርን ስም የማጠልሸት እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች ፣ ይሄን ተከትሎ ዮናይትድ ስቴትስ የያዘችው አቋም ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉ ነቀፈውታል።

ይህ በአንዲህ እንዳለ የዮናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን በትናንትናው ዕለት በውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሸንጎ ፊት ባቀረቡት ማብራሪያ ፣ በምዕራብ ትግራይ “የዘር ማጽዳት ” ወንጀል መፈጸሙን አመላክተዋል። በክልሉ ውስጥ ያለውን " ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ የገለጹትን ሁኔታ ለማሻሻል ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችንም ጠቁመዋል።

የረድኤት ድርጅቶች እና ሰራተኞቻቸውን በክልሉ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ፣ በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦችን ደህንነት መጠበቅ ከተጠቆሙት መደረግ የሚገባቸው እርምጃዎች መካከል ናቸው።ወደ ክልሉ ሰላም አስከባሪ ለመላክ ሀሳብ ይኖር እንደሁ በአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ከረን ባዝ የተጠየቁት ብሊንከን ፣የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከክልሉ ወጥተው “የትግራይን ህዝብ ሰብአዊ መብት የማይጥስ ፣ በምዕራብ ትግራይ ያየነውን የዘር ማጽዳት የማይፈጽም ኃይል” መተካት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

ሙሉ ዘገባውን ያዳምጡ፦

Your browser doesn’t support HTML5

የአሜሪካን ኢትዮጵያን የሚመለከት ወቅታዊ አቋም ያወገዘ ሰልፍ ተደረገ