የኤርትራ የልዑካን ቡድን በሱዳን

  • ቪኦኤ ዜና

በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ እና በፕሬዚደንታዊ አማካሪው አቶ የማነ ገብረአብ የተመራ የኤርትራ ልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት በካርቱም ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ከጄኔራል አብደልፋታህ አል ቡርሃን ጋር ተገናኝቷል።

ልዑካኑ የኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሣያስ አፈወርቂ የሱዳንን እና የኢትዮጵያን ግንኙነቶች አስመልክተው የላኩትን መልዕክት ለሱዳኑ መሪ የላኩትን መልዕክት አድርሰዋል።

ይህንኑ መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አብደላ ሃምዶክም ማድረሳቸውን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሣያስ አፈወርቂ ለሱዳን መሪዎች በላኩት ደብዳቤአቸው ሁለቱ ጎረቤት ሃገሮች ልዩነቶቻቸውን በመግባባት እና በትዕግሥት መፍታት ያለባቸው መሆኑን አጥብቀው ማሳሰባቸውን ነው የጠቆሙት።

የሱዳን ፕሬዚደንት አል ቡርሃን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ኤርትራ በዚህ ረገድ እያደረገች ስላለው ያልተቋረጠ ጥረት ምስጋና ማቅረባቸውን የአቶ የማነ ገብረ መስቀል የትዊተር መግለጫ ጨምሮ አመልክቷል።

አስከትለውም የሱዳን ፕሬዚደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃገራቸው ጊዜያዊ ዕክሎችን በሰላማዊ መንገድ ፈትታ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመመስረት ብሎም ለቀጣናዊ ትብብር ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸውላቸዋል ብለዋል።