በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የመምህራን ደመወዝ በመከፈሉ በወላይታ ዞን የተቋረጠው ትምህርት ተጀምሯል


የመምህራን ደመወዝ በመከፈሉ በወላይታ ዞን የተቋረጠው ትምህርት ተጀምሯል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:16 0:00

የመምህራን ደመወዝ በመከፈሉ በወላይታ ዞን የተቋረጠው ትምህርት ተጀምሯል

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን፣ ላለፉት ሁለት ወራት ያህል ታጉሎ የቆየው የመምህራን ደመወዝ በመከፈሉ የተቋረጠው የመማር ማስተማር ሒደት መቀጠሉን፣ የክልሉ የመምህራን ማኅበር አስታወቀ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዐማኑኤል ጳውሎስ፣ ችግሩ ተፈጥሮባቸው የነበሩት የአንድ ከተማ አስተዳደር እና የ20 ወረዳዎች ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ውስጥ የሚያስተምሩ የአካባቢ ሳይንስ መምህር፣ ለሁለት ወር ያህል የታጎለባቸው ደመወዝ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በመከፈሉ ከሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. አንሥቶ ተቋርጦ የቆየው ትምህርት መቀጠሉን በስልክ ለአሜሪካ ተናግረዋል፡፡

መምህራን ወደ ሥራቸው የተመለሱት፣ የሁለት ወር ደመወዛቸው በከፊል እና ሙሉ በሙሉ በመከፈሉ መኾኑን፣ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን ሌላው መምህር ገልጸዋል፡፡

ደመወዛቸው ለሁለት ወራት ያህል መቋረጡ መምህራኑን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቡናዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች እንዳጋለጣቸው መናገራቸውን ፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ ዘገባችን ማስደመጣችን ይታወሳል፡፡

አሁንም ችግሩ በዘላቂነት ለመፈታቱ ጥርጣሬ እንዳላቸው ያልሸሸጉት መምህራኑ፣ የባከነውን የትምህርት ሰዓት ለማካካስ ተግተው እንደሚሠሩ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዐማኑኤል ጳውሎስ፣ የመምህራኑ ውዝፍ ደመወዝ መከፈሉን ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ አረጋግጠዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሒደቱ በተቋረጠባቸው ኹሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት መቀጠሉን የተናገሩት አቶ ዐማኑኤል፣ ችግሩ የተፈታው በጊዜያዊነት መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

መሰል ችግር በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ከቀጠለ፣ በተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግለት አበክረው ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ ከሚገኙ ስድስት የከተማ አስተዳደሮች እና 17 ወረዳዎች ውስጥ 16ሺሕ753 መምህራን የሚገኙ ሲኾን፣ የደመወዝ ክፍያ ችግሩ ያጋጠመው በአንድ የከተማ አስተዳደርና በ20 ወረዳዎች ውስጥ እንደነበረ፣ የመምህራን ማኅበሩን ፕሬዚዳንት ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ፣ በዚኹ በወላይታ ዞን ደመወዝ ያልተከፈላቸው ሌሎችም የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሁለት ወራት ውዝፍ ደመወዛቸው 70 በመቶ መከፈሉን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዞንን ጨምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚስተዋለው የደመወዝ ክፍያ ችግር እና የበጀት እጥረት፣ ከአዲስ ክልል ምሥረታ ጋራ የተያያዘ መኾኑ ተገልጿል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG