በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳሰበ


ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ወንዙን አቋርጠው ወደ ሱዳን በመሰደድ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን
ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ወንዙን አቋርጠው ወደ ሱዳን በመሰደድ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን

የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አሳሰበ። የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በላኩት መግለጫ፤ ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ዘረፋ፣ መደፈር፣ እና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ ታማኝ ከሆኑ ሪፖርቶች ተሰምቷል ብለዋል። አያይዘውም “በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞችን የኤርትራ ወታደሮች በኃይል ወደ ኤርትራ እየመለሷቸው ስለመሆኑ ማስረጃ አለ” ብለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተጽፎ የወጣው መግለጫ፤ ከአፍሪካ በ114 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛቷ ከፍተኛነት ሁለተኛ የሆነችውን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ በሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሦስት ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ክልል ጦርነት ተዋናይ በሆኑ አካላት ላይ አዲሱ የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር የሚያደርገውን ግፊት የሚያሳይ ነው ሲል ኤፒ በዘገባው አስነብቧል።

“ በአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ካልተንቀሳቀሰ በመቶ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ በሚለው ጉዳይ “ስጋት አለን” ብሏል። 

አሶሼትድ ፕሬስ ከትግራይ ክልል የወጡ የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ባጠናቀረው ዘገባ፤ የኤርትራ ወታደሮች ዘረፋ እንደሚፈፅሙ፣ ቤት ለቤት እየተዟዟሩ ሰዎችን እንደሚገድሉ እና ልክ እንደ አካባቢው አስተዳዳሪ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሃገር ከድተዋል ተብለው የሚታመኑትን የትግራይ አመራሮች ለመያዝ በሚያደርገው ውጊያ ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች ተሳትፈዋል ያለው ዘገባው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች መሳተፋቸውን ሙሉ ለሙሉ ማስተባበሉን ጠቅሷል።

ተደረጉ በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ገለልተኛ እና ግልፅ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ የሚጠይቀው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ መግለጫ፤ “የት እና ምን ያህል የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ እንደሚገኙ አልታወቀም” ብሏል። ሆኖም ይህን ጥያቄ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በቀጥታ ለኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት አቅርቦት እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጽ/ቤት እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጠው ምላሽ የለም።

የዓይን እማኞች ግን በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ የገለፁ ሲሆን፤ የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ምላሽ የለም። ሆኖም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በትዊተር ገፅ ላይ እንደሰፈረው ፤ “በኤርትራ መንግሥት ላይ የሚደረገው የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደገና እየጨመረ ነው” ብሎታል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ሌላው ከታማኝ ዘገባዎች እንደተረዳው ገልፆ አሳሳቢ እንደሆነ የጠቀሰው ጉዳይ፤ በትግራይ ክልል ውስጥ የምግብ እጥረት መከሰቱን ሲሆን፤ “ በአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ካልተንቀሳቀሰ በመቶ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ በሚለው ጉዳይ “ስጋት አለን” ብሏል።

በሌላ በኩል በቅርቡ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃ ደስታ፤ በክልልሉ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልፀው፤ ያለውን ምግብ በሚገባ ለማከፋፈል ደግሞ አሽከርካሪዎች የፀጥታ ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በመሆኑም ኮማንድ ፖስት በማቋቋም በእጀባ እርዳታውን ለማድረስ በዝግጅት ላይ እንዳሉ አስታውቀዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:34 0:00


XS
SM
MD
LG