በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን የሚካሄደው ጦርነት የረሃብ አደጋን ደቅኗል


ፎቶ ፋይል፦ግጭቱን ሸሽተው አድሬ በሚገኘው ኦውራንግ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሱዳናውያን ውሃ ለመቅዳት ወረፋ ያዘው እአአ ታኅሣስ 7/2023
ፎቶ ፋይል፦ግጭቱን ሸሽተው አድሬ በሚገኘው ኦውራንግ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሱዳናውያን ውሃ ለመቅዳት ወረፋ ያዘው እአአ ታኅሣስ 7/2023

በሱዳን በመካሄድ ላይ ያለው የሁለት ጀኔራሎች ጦርነት ከካርቱም በስተ ደቡብ ወደምትገኘውና አል-ጃዚራ ወደተሰኘችው ለም አካባቢ ከተዛመተ ወዲህ፣ በአንድ ወቅት ትርፍ ያመርቱ የነበሩ ገበሬዎች ምጽዋት ጠባቂ ሆነዋል።

ገበሬዎቹ ወደ ማሳቸው መሄድ እንዳልቻሉ እና የዘሩትን መንከባከብም ሆነ መሰብሰብ እንዳልቻሉ ለኤ.ኤፍ.ፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

በሱዳን መደበኛ ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ባለፈው ሚያዚያ ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ፣ አል-ጃዚራ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች መጠለያ እንደሆነበረች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ጦርነቱ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እየተስፋፋ በመምጣቱ ግን፣ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር በአል-ጃዚራ የነበረው ሰላም ደፍርሷል። ዋድ ማዳኒ የተሰኘችውን ከተማ ለመቆጣጠር ውጊያው በመፋፋሙ፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ለመሸሽ ተገደዋል።

የሱዳን ሠራዊት ዋድ ማዳኒን ጥሎ ሲወጣ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሰፊ የእርሻ መሬቶችን በመቆጣጠሩ፣ ሰዎች መንደራቸውን ለቆ ለመውጣትም ሆነ በመስኖ እና ማዳበሪያ የሚለሙ ሰፋፊ እርሻዎቻቸውን ለመንከባከብ እንዳይቹሉ አድርጓል።

የተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደሚለው፣ በአሁኑ ወቅት 18 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከረሃብ ጋር ተፋጠዋል። አምስት ሚሊዮን የሚሆኑቱ ደግሞ አስቸኳይ መልስ የሚያሻው ሁኔታ ውስጥ ናቸው።

ረሃብ በይፋ ባይታወጅም፣ መከሰቱ አይቀሬ መሆኑን ‘የኖርዌ ፍልሰተኞች ም/ቤት’ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲያስታውቅ፣ የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤይድ) በበኩሉ፣ ጦርነቱ ሰብል አምራች በሆኑ አካባቢዎች መስፋፋቱ፣ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ እንደጣለ አመልክቷል።

በሱዳን ዘጠኝ ወራት ያስቆጠርውን ጦርነት ለማስቆም እና የሰብዓዊ ሥራ ለማከናወን እንዲቻል፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “አስቸኳይ እና ወሳኝ” እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የተመድ የአስቸኳይ ግዜ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ባለፈው ሐሙስ አሳስበዋል።

በዚህ ዓመት ሃያ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሱዳናውያን ርዳታ እንደሚያሻቸው የጠቀሱት ኃላፊው፣ ውጊያው የሚቀጥል ከሆነ ግን ርዳታ የማድረስ ሥራው እንደሚስተጓጎል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG