በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኮሬ ዞን በቀጠለው ጥቃት አራት አርሶ አደሮች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለፀ


በኮሬ ዞን በቀጠለው ጥቃት አራት አርሶ አደሮች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለፀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:30 0:00

በኮሬ ዞን በቀጠለው ጥቃት አራት አርሶ አደሮች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለፀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ፣ አራት ወጣት አርሶ አደሮች፣ ከምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ በተነሱ ታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

በእርሻ ሥራ ላይ እንደነበሩ የተገለጹት አርሶ አደሮች የተገደሉት፣ “ኦነግ ሸኔ” ባሏቸው ታጣቂዎች እንደኾነ፣ የኮሬ ዞን የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈራ ቦንዶራ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ቆቦ ቀበሌ ትላንት ሚያዚያ 13 ተገደሉ ከተባሉ አራት ወጣት አርሶ አደሮች ውስጥ ሁለቱ የወንድማቸው ልጆች እንደኾኑ አቶ ምትኩ ሽብሩ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ገልፀዋል።

አራቱም የሁለት ቤተሰብ አባላት መኾናቸውን፣ የሟቾቹን ስም በመዘርዘር የገለፁት አቶ ምትኩ እርስ በርሳቸውም ዘመዳማቾች መኾናቸውን አክለዋል። ለጥቃቱ ጉጂ ዞን ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ ያሏቸውን ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደረጉት አቶ ምትኩ፣ ይህን የሚያስቆም ኃይል ባለመኖሩ ሕዝቡ ስጋት ላይ መውደቁን ገልፀዋል።

አቶ አጋፋሪ መንገሻ የተባሉ የቆቦ ቀበሌ ነዋሪ የእርሻ ማሳቸውን አረም በሚያርሙበት እና ከብቶቻቸውን በሚጠብቁበት ወቅት እንደተገደሉ ተናግረዋል።

አቶ አጋፋሪ ተዘርፈዋል የተባሉ ከብቶች እና ሌሎች ንብረቶች ወደ ገላን ወረዳ እንደተወሰዱባቸው ገልፀው ክስ አሰምተዋል። ባለፈው ሳምንት የ13 ዓመት አዳጊ እና ሌላ አርሶ ከቆቦ ቀበሌ መገደላቸውን አቶ አጋፋሪ አስታውሰዋል።

የኮሬ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈራ ቦንዶራ በግብርና ሥራቸው ላይ የነበሩ አራት አርሶ አደሮች የተገደሉት ሸኔ ሲሉ በጠሯቸው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች መኾኑን ተናግረዋል።

አቶ ተፈራ አክለው ካለፈው ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም ጀምሮ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሰባት አርሶ አደሮች ዳኖ ፣ መቅሬዲ እና ቆቦ ከተሰኙ ቀበሌዎች ያልታጠቁ ሲቪሎች በታጣቂዎች መገደላቸውን አክለው ገልጸዋል::

ስለ ጉዳዩ ከአፋን ኦሮሞ ክፍል ባልደረባ ነሞ ዳንዲ የተጠየቁት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም፣ በዓለም አቀፍ ቃል አቀባዩ አቶ ኦዳ ተርቢ ክሱን አስተባብለዋል። ከምዕራብ ጉጂ ዞን ባለሥልጣናት አስተያየትና ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም::

ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ጉዳይ የተጠየቁት የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ቀበሌዎቹ በሸማቂዎች በሚደርሰው ጥቃት የተነሳ ከቁጥጥር ውጭ መኾኑና ለኅብረተሰቡ መግሥታዊ አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ መናገራቸው ይታወሳል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG