በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከተደረመሰው ሕንጻ በሕይወት የተረፉትን ፍለጋው ቀጥሏል


የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከተደረመሰው ሕንፃ ሥፍራ በሥራ ላይ ጆርጅ፣ ደቡብ አፍሪካ
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከተደረመሰው ሕንፃ ሥፍራ በሥራ ላይ ጆርጅ፣ ደቡብ አፍሪካ

የአደጋ ሰራተኞች ዛሬ ማክሰኞ በደቡብ አፍሪካዋ የጆርጅ ከተማ ለበርካቶች ሞት ምክኒያት ከሆነው የሕንጻ መደርመስ አደጋ የተረፉትን ለማዳን በመሯሯጥ ላይ ናቸው። ባሉበት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከፍርስራሹ ስር የሚገኙ 11 ሰዎችን ማነጋገር መቻላቸውንም ጨምረው አመልክተዋል።

ትላንት ሰኞ ከኬፕ ታውን ከተማ በስተምስራቅ 400 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጆርጅ አምስት ፎቆች ያሉት ሕንፃ በተደረመሰበት ወቅት በፍርስራሽ የተቀበሩ 27 ሰዎችን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ቆፍረው ማውጣታቸውን የከተማይቱ ማዘጋጃ ቤት ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ከእነኚህም ውስጥ ስድስቱ ህይወታቸው ማለፉን አክለው ተናግረዋል። እስካሁን ያልተገኙት ሰዎች ቁጥር 48 መሆኑንም ኬፕታዋን ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቹ ተጠሪ ኮሊን ዲነር አስታውቀዋል።

ከምድር በታች የሚገኝ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ጋራዥን ጨምሮ ለሕንጻው መፈራረስ መንስኤው ምን እንደሆን እስካሁን በውል አልታወቀም። አደጋውን ተከትሎ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለተጎጂዎች "ለዘመዶች እና ወዳጆቻቸው" ያደረባቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀው፡ ሁሉንም አስባችኋለሁ ብለዋል።

አያይዘውም “ህብረተሰቡን መልስ እንዲያገኝ እና ይህን መሰሉ አደጋ እንዳይደገም” ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል። ቁጥሩ 160, 000 የሚጠጋ ህዝብ መኖሪያ የሆነችው ጆርጅ በደቡባዊ የሃገሪቱ የባሕር ጠረፍ የምትገኝ በቱሪስት መስመር ላይ የምትገኝ ውብ የባሕር ዳርቻ ከተማ ናት።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG