በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፖሊስ ከበቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋራ በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታወቀ


ፖሊስ ከበቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋራ በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:39 0:00

ፖሊስ ከበቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋራ በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታወቀ

በምሥራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ጠዋት ተገድለው ከተገኙት የኦነግ ከፍተኛ አመራር አቶ ቤቴ ዑርጌሳ ኅልፈት ጋራ በተያያዘ፣ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገለጸ።

መንግሥታዊ ብዙኀን መገናኛዎች፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መመሪያ አዛዥን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት፣ እስከ አሁን ተደረገ በተባለው ክትትል 13 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በዚኹ ጉዳይ ላይ፣ የአሜሪካ ድምፅ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ እና ከመቂ ከተማ ፖሊስ ኃላፊዎች ለማጣራት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

በሌላ ዜና፣ ሁለት የአቶ በቴ ቤተሰብ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁና የቅርብ ዘመድ ነኝ ያሉ ምንጭ ፤“ትላንት ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ፣ አንድ የበቴ ዑርጌሳ ወንድም እና አንድ እህቱ በፖሊስ ተይዘው ነበር። የበቴ እህት ፣ስምቦ ዑርጌሳ አንድ ሰዓት አካባቢ ተለቃለች፤። ወንድሙ ግን ፈጣን መንገድ በሚባለውና ገብርኤል አካባቢ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ተወስዷል።” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

አቶ ሚሎ ለምን በቁጥጥር ሥር ሥር እንደዋሉ፣ እስከአሁን ለቤተሰቡ አባላት የተገለጸ ነገር አለመኖሩን፣ እኚኹ የቅርብ ዘመድ አክለው ተናግረዋል።

በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸው የአቶ በቴ ዐርጌሳ ወንድም አቶ ሚሎ ዑርጌሳ፣ ስለ ግድያው ለአሜሪካ ድምፅ መናገራቸው ይታወሳል።

የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ማውገዛቸውን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ግድያው በፍጥነት፣ በጥራት እና በምልዓት እንዲጣራና ተጠያቂዎች ተለይተው ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል። አምባሳደር ኮቢያ፣ ከአቶ በቴ ግድያ ጋራ በተያያዘ የሕግ ተጠያቂነት መረጋገጡ፣ ለቀጣይ እርቅ እና ስምምነት መንገድ የሚከፍት ነው፤ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር እና በአፍሪካ ኅብረት የዩናይትድ ኪንግደም ተወካይ አምባሳደር ዳረን ዌልች፣ ግድያውን በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው አውግዘዋል፡፡ “የግጭት አዙሪት” ሲሉ ለገለጹት የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ችግር የፖለቲካ ውይይት እንደሚያስፈልግ አንሥተዋል፡፡ ለመሰል ግድያዎች ፍትሕ መስጠት ለንግግር መንገድ ከፋች ከኾኑ ርምጃዎች አንዱ እንደኾነም ጠቁመው፣ የአቶ በቴ ዑርጌሳ ገዳዮች ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል፤ ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ቢሮ እና የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ፣ከአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋራ በተያያዘ ለሕግ ተጠያቂነት መረጋገጥ ጥሪ የሚያቀርቡ መግለጫዎችን ማውጣታቸው ይታወሳል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG