በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ድርቅ የብሄራዊ አደጋ ሥጋት የደቀነባት ማላዊ የርዳታ ጥሪ አሰማች


 የማላዊው ገበሬ በበቆሎ ማሳቸው ውስጥ ሲዘዋወሩ ዋና ከተማዋ አካባቢ ሊሎንግዌ፣ ማላዊ
የማላዊው ገበሬ በበቆሎ ማሳቸው ውስጥ ሲዘዋወሩ ዋና ከተማዋ አካባቢ ሊሎንግዌ፣ ማላዊ

በተፈጥሮ የሚከሰተው ኤልኒኞ፣ በፓስፊክ ምሥራቃዊ ውቅያኖስ አካባቢ ከሚታየው ያልተለመደ የውሃ ግለት የሚነሳው ሙቅ አየር በዓለም ዙሪያ የአማካይ ሙቀት መጠን እንዲጨምር በማድረጉ እና እንዲሁም ወደ ከባቢ ዓየር የሚለቀቀው በካይ የካርቦን መጠን የከሰቷቸው ሁኔታዎች ተደራርበው ድፍን ደቡባዊ አፍሪቃ ባለፉት ዓመታት አጋጥሞት በማያውቅ አስከፊ ድርቅ እየተናጠ ይገኛል። ይህንንም ተከትሎ ማላዊ፣ ዝምባብዌ እና ዛምቢያ ባለፈው ወር አከባቢውን በመታው ድርቅ ሳቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል።

የምግብ አቅርቦት ምንጮች እየነጠፉ ባሉባት ማላዊ፡ የማሳ ሰብል ስርቆት ብርቱ ችግር እየሆነ ነው። የበቆሎ አምራች የነበሩ ኡላሊያ ላፑሶኒ የተባሉ አንዲት ገበሬ ሲናገሩ፡ በድርቁ ሳቢያ የዘሩት በቆሎ ባለማፍራቱ በአሁኑ ወቅት የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

"እስኪ አስቡት ለዚህ ወር የሚሆን ምግብ የለንም፤ እንዴ አድርገን ተርፈን እስከሚቀጥለው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ መድረስ እንችላለን? ከባድ ነው የሚሆነው” ብለዋል የደረቀ ማሳቸውን እያሳዩ።

ከዚሁ በተያያዘም፡ የማላዊው ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ሃገራቸውን ከረሃብ አደጋ ለመታደግ አለም አቀፍ ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል። በዓለም ዙሪያ በ2023 አዲስ ሪከርድ ያስመዘገበው የአየር ንብረት ለውጥ ኤልኒኞ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ማባባሱም ተዘግቧል።

ዓለም አቀፉ የረድኤት ድርጅት ኦክስፋም ባለፈው ሳምንት እንዳስጠነቀቀው፡ በደቡባዊ አፍሪቃ ከ24 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በድርቅ ሳቢያ ለረሃብ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የውሃ እጥረ ተጋልጠዋል።

በማላዊ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያም ‘ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተጎድተዋል’ ሲል ዩኒሴፍ አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG