በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ተኩሶ በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ


ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ 
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ 

በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በቀጥታ ተሳታፊ ናቸው በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ አቶ ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ አርቲስቱን በቀጥታ ተኩሶ በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ መታሰሩን ተናግረዋል።

ሁለተኛው አብዲ አለማየሁ የተባለው ግለሰብ ደግሞ በተባባሪነት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች ከበደ ገመቹ የተባለ ሦስተኛ ተጠርጣሪ እየተፈለገ መሆኑን ጥቆማ ። አያይዘውም አንደኛ ተጠርጣሪ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ቃል ድርጊቱን የፈፀመው፤ “ኦነግ ሸኔ” ከተባለው ክንፍ በተሰጠው ተልኮ መሆኑን መግለፁን አስረድተዋል።ተልኮውን የሰጡት ግለሰቦችም ሁለት መሆናቸውን አምኖ መቀበሉን ገልፀዋል። መንግሥት ኦነግ ሸኔ እያለ የሚጠራቸውና ራሳቸውን “የኦሮሞ ነፃነት ጦር” ብለው የሚጠሩት በጫካ በውጊያ ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ቡድኖች ከመንግሥት ለሚቀርብባቸው ክስ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በቅርቡ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ክንፍ በጫካ ቀርቶ የሚዋጋውና በከተማ ውስጥ ሽብር የሚፈጥረው “ኦነግ ሸኔ” መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ራሳቸውን “አባ ቶርቤ” ብለው የሚጠሩ በየከተማው እየገቡ አደጋ የሚያደርሱም አሉ ብለዋል። የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና በደረሰው ጥቃት እስካሁን 177 ሰዎች መገደላቸውን ፌደራል ፖሊስ አረጋግጧል። በዚህ ድርጊት ተጠርጥረው የተያዙ ወደ 4,700 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም መንግሥት አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG