በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም ታላላቅ ከተሞች ፀጥታ ጥበቃቸውን አጠናክረዋል


የቱርኳ ከተማ አንታሊያ ላይ የተካሄደው የቡድን ሃያ ጉባዔ ቀደም ሲል ታቅዶ የነበረው በንግድ፣ በኢነርጂና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለመነጋገር የነበረ ቢሆንም የፓሪሱ የሽብር ጥቃት ግን የጉባዔውን ሙሉ ትኩረት ቀይሮታል፡፡

ፓሪስ ላይ የተፈፀመው ጥቃት “በሥልጡኑ ዓለም ላይ የተፈፀመ ነው” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሃያዎቹ የበለፀጉ ሃገሮች ጉባዔ ላይ ዛሬ ተናግረዋል፡፡

የቱርኳ ከተማ አንታሊያ ላይ በተካሄደው የቡድን ሃያ ጉባዔ ቀደም ሲል ታቅዶ የነበረው በንግድ፣ በኢነርጂና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለመነጋገር የነበረ ቢሆንም የፓሪሱ የሽብር ጥቃት ግን የጉባዔውን ሙሉ ትኩረት ቀይሮታል፡፡

ለጥቃቱ ከየአካባቢው እየተሰጠ ያለው ምላሽና ሥጋቱም አሁንም እንደቀጠሉ ሲሆን ለጥቃት ሊጋለጡ ይችላሉ በሚባሉ የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ የፀጥታ ጥበቃው እንዲጠናከር ተደርጓል፡፡

ከሁሉም የበዛው የሕይወትና የአካል ጉዳት እንዲደርስ የተደረገበትን የባታክላን የሙዚቃ ዝግጅት አዳራሽ ጨምሮ በስድስት የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ በፍንዳታ፣ በተኩስ እና በአጥፍቶ መጥፋት እርምጃ የታጀቡ ጥቃቶች ናቸው ፓሪስን የዋጧት - የከትናንት በስተያው ዐርብ ምሽት ላይ፡፡

ውቢቱ ፓሪስ ወደ ጦር አውድማነትና የጥፋት መስክነት የተለወጠች መሰለች፡፡

የነፃነት፣ የእኩልነትና የወንድማማችነት አስተሳሰስና እሴት እናትና ማዕከል የሆነችው ፈረንሣይ በድጋሚ በሽብር ተመታች፡፡ ዓለም እንደገና ደነገጠ፡፡

የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ “የጦርነት አድራጎት ነው” ብለውታል ጥቃቱ እንደተፈፀመ የሃገራቸውና የጀርመን ቡድኖችን ኳስ ይመለከቱ ከነበሩበት የፓሪሱ ስታዲየም በፀጥታ ሰዎቻቸው ተፋፍሰው እየተወሰዱ ሳሉ፡፡

አንታሊያ-ቱርክ ላይ ዛሬ ተሰብስበው እየተነጋገሩ ያሉት የዓለም እጅግ ኃያል እና እጅግ ባለጠጋም ሃገሮች መሪዎች ዛሬ እንዲህ የሚሉ ቃላትን ያዘለ መግለጫ አወጡ፡-

ፓሪስ ውስጥ የተፈፀሙትን አስደንጋጭና አስቀያሚ የሆኑ ጥቃቶች ተተካካይ በሌለው እጅግ ብርቱ የሆነ መግለጫ እናወግዛለን፡፡ ለመላው ሰብዕና ተቀባይነት የሌላቸው ስድብ ናቸውና፡፡ ሽብር ፈጠራን በምንም መልኩና መቼም ይፈጠር ልንዋጋው ያለንን መደጋገፍና ፅናት በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡

መሪዎቹ በመካከላቸው የስለላ መረጃ ልውውጥን ለማጠናከር፣ ብሔራዊ ወሰኖቻቸውን ለማጥበቅ፣ ለሽብር ፈጠራ አድራጎት የሚጎርፈውን ገንዘብ ለማስቆም እንደሚሠሩ ዛሬ በድጋሚ ቃል ተገባብተዋል፡፡

ፈተናውን መጋፈጥ የሚቻለው በጦር መንገድ ብቻ እንዳልሆነና በርካታ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ተስማምተናል፡፡ብለዋል የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን እነዚህን ሰይጣኖች ለመውጋት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ማድረግ የነበረብን ቢሆንም አሁንም ኃይሎቻችንን በጋራ ማቀናጀት አለብን ብለዋል፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረን ቢሮ ማምሻውን እንዳስታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን ከቡድን ሃያ ዋና ስብሰባ አዳራሸ ወጣ ብለው ተነጋግረው ነበር፡፡ እናም ሞስኮ በእሥላማዊ መንግሥት ቡድን ላይ እያካሄደች ያለችውን ድብደባና ጥቃት አጠናክራ እንደምትቀጥል ፑቲን ቃል ገብተዋል፡፡

ከሁለተኛው የዓለም ጣርነት ወዲህ ሲከሰት በግዝፈቱ የመጀመሪያው ነው ለተባለው ለሦሪያ የስደት ቀውስ ምግብና ድጋፍ ለማሰባሰብ ከፊታችን በሚመጣው በአዲሱ አውሮፓ ዓመት ውስጥ እንግሊዝ ውስጥ አንድ ግዙፍ የለጋሾች ጉባዔ እንደሚጠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ካምረን ማምሻውን ለጋዜጠኞች ነግረዋል፡፡

ጥቃቱ ከተፈፀመ አንስቶ የሃገራቸውን አቋም ሲያሣውቁ የቆዩት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሦሪያ ቀውስ እንዲያበቃ ለማድረግና ፈረንሣይ ጥቃት አድራሾቹን ለመያዝ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ ጥረታቸውን በእጥፍ ድርብ እንደሚያሳድጉ ቃል ገብተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ራቺብ ጣዪብ ኤርዶሃን ጋር ከተወያዩ በኋላ ጥረቶቻችንን በእጥፍ ድርብ እናሳድጋለንብለዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ከፈረንሣዊያን ጋር በአጋርነት እንደምትቆም፤ አጥቂዎቹን አብራ እንደምታሳድድና የሦሪያ ቀውስ እንዲያበቃ እንደምትሠራ ተናግረዋል ኦባማ፡፡

አንካራ ውስጥ እንደተፈፀመው አስከፊ ጥቃት ሁሉ በተንሻፈፈ አስተሳሰብ በመነሣሣት ምክንያት ንፁሃን፤ ምስኪን ሰዎች መገደላቸው በፈረንሣይ ላይ ወይም በቱርክ ላይ ብቻ የተፈፀመ ጥቃት አይደለም፡፡ በመላው የሠለጠነ ዓለም ላይ እንጂ፡፡ብለዋል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት፡፡

የቡድን ሃያ ጉባዔ የተከፈተው መሪዎቹ ለተገደሉት የኅሊና ፀሎት አድርገው ነበር፡፡

129 ሰው የተገደለበትን የፓሪስ ጥቃት ያደረስኩት እኔ ነኝ ሲል ‘እሥላማዊ መንግሥት ነኝ’ የሚለው ቡድን ፈጥኖ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡

ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ቢያንስ እስከፊታችን ሐሙስ ኃይል ላይ የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በመላ ሃገሪቱ አውጀዋል፡፡

ሌሎችም ጥቃቶች ሊፈፀሙ ይችላሉ በሚል ሥጋት ባለሥልጣናቱ በመላ ፈረንሣይ ፀጥታ አስከባሪዎችን አሠማርተዋል፡፡

በፓሪስ ላይ በተፈፀሙት ተደራራቢ ጥቃቶች ኀዘናውንና ንዴታቸውን የገለፁ የዓለም መሪዎች ከፈረንሣይ መንግሥትና ሕዝብ ጎን እንደሚቆሙ ያሳወቁት ጥቃቱ ከተፈፀመበት ምሽት አንስቶ ነበር፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንዲህ ነበር ያሉት፤ ፈረንሣይ የጥንት ወዳጃችን ነች፡፡ የፈረንሣይ ሕዝብ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በተደጋጋሚ ትከሻ ለትከሻ ቆሟል፡፡ እኛም እነርሱ ከሽብርተኝነትና ከፅንፈኝነት ጋር እያደረጉ ባሉት ጦርነት ከጎናቸው እንቆማለን

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝም ጥቃቱ እንደተፈፀመ ኀዘናቸውን ከገለፁት መሪዎች አንዱ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፐሬሽን ዘግቧል፡፡

ለፈረንሣዩ ፕሬዚዳንት እየደወሉም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን ባደረጓቸው ንግግሮች ኀዘናቸውንና ቁጣቸውን ከገለፁት መሪዎች መካከል የቫቲካን ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ይህ አድራጎት በማንኛውም ሃይማኖትም ይሁን በሰው ዘንድ ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል ይህ ጥቃት በነፃነት ላይ የተፈፀመው በፓሪስ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁላችንም ላይ ነው፤ ሁላችንንም ይጎዳናል፡፡ ለዚህም ነው መልሱን ሁላችንም አብረን የምንሰጠውብለዋል፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረን የእሥላማዊ መንግሥት ቡድንን ታጣቂዎች ጨካኝና ርኅራሄ የለሽ ነፍሰ ገዳዮች ሲሉ ጠርተዋቸዋል፡፡ ሃገራቸው “መርዛማና ፅንፈኛ” ያሉትን አስተሳሰብ ለማጥፋት ጥረቷን እንደምታጠናክር ዝተዋል፡፡

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የውንብድና አድራጎት ብለውታል፡፡

በኢራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮውሃኒ በአውሮፓ ሊያደርጉት አቅደውት የነበረውን የአራት ቀናት ጉብኝት ሠርዘው ጥቃቶቹን በሰብዕና ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ብለዋቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን አሣፋሪ የሽብር ጥቃቶች ብለዋቸዋል፡፡

የሦሪያው ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ በመላ ሰብዕና ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው ሲሉ አውግዘውታል፡፡

ሂዝቦላ የሚባለው ቡድንም የፓሪሱን ጥቃት አውግዞ ሰሞኑን እሥላማዊ መንግሥት ቡድን ሊባኖስ ውስጥ ለፈፀመው የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እንደሚበቀል ዝቷል፡፡

የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ተስክ ለፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ በፃፉት ደብዳቤ ፓሪስ ላይ የተፈፀመው አሣዛኝና ወራዳ የሽብር አድራጎት ሊከፋፍለን፣ ሊያስደነብረንና ፈረንሣይን ታላቅ መንግሥት የሚያደርጓትን እሴቶች ነፃነትን፣ እኩልነትን፣ ወንድማማችነትን ሊጠፋ እንደማይችል፤ በዚህም ዒላማውን እንደማይመታ እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡

የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ዛሬ ለተካሄደው የቡድን ሃያ ስብሰባ ወደ ቱርክ ሊያደርጉ የነበረውን ጉዞ መሠረዛቸውን ወዲያው አሳውቀው እንዲህ አሉ፤

ሽብርተኞች እንዲህ ዓይነቶቹን የጭካኔ አድራጎቶች ሲፈፅሙ፣ ከፊታቸው ተደቅና የሚያገኟት በቁርጠኝነቷ የፀናች ፈረንሣይን፣ አንድ ፈረንሣይን፣ የተሰበሰበች ፈረንሣይንና እራሷን ለመሸማቀቅ ያላሣደረች ፈረንሣይን እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል

በሌላ በኩል ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ዋና ዋና በሚባሉ ሰዉ በርከት እያለ ሊገኝ በሚችልባቸው አይሮፕላን ጣቢያዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያና የውድድር ሥፍራዎችንና የሙዚቃ ትርዒትና ሌሎችም የመዝናኛ ክንዋኔዎች የሚቀርቡባቸውን አዳራሾችና አካባቢዎች እንዲሁም ትላልቅ ከተሞቿን ለመጠበቅ የፀጥታ ሥምሪቷን አጠናክራለች፡፡

የሎስ አንጀለስ ከንቲባ ኤሪክ ጋርሴቲ ከተማይቱ አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ እርምጃዎችን ሁሉ መውሰዷን ተናግረዋል፡፡

ከሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጄ ጆንሰን ጋር በስልክ ተነጋግረናል፡፡ ሁሉንም የስለላና ቅኝት ሥራዎች እያጠናከርን ነው፡፡ ዐይናችንን ከፍተን መጠበቅ አለብን፡፡ብለዋል ጋርሴቲ

በዩናይትድ ስቴትስ እጅግ ግዙፉ የገበያ ማዕከል የሚገኘው በሚኔሶታ ውስጥ ነው፡፡ ባለፈው የካቲት የተለየ ዛቻ ስለደረሰበት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፀጥታና የደኅንነት ጥበቃው የተጠናከረ ነው፡፡

የኒው ዮርክ ከተማ የፖሊስ ኮሚሽነር ሬይ ኬሊ ማድረግ የሚችሉት ሁሉ ገደብ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ለጥቃት የተጋለጡ ሥፍራዎች ያሉት እዚህም እዚያም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለንብለዋል፡፡

አሜሪካዊን ግን በአብዛኛው የየአካባቢዎቻቸው የፀጥታ ሠራተኞችና ባለሥልጣናት ከአደጋ እንደሚጠብቋቸው መተማመናቸውን ይገልፃሉ፡፡ በመሆኑም መደበኛ እንቅስቃሴዎቻቸውንና ተግባራቸውን የማስተጓጎል ወይም የማቋረጥ ሃሣብ የላቸውም፡፡

አሜሪካዊያንም በሌሎች የዓለም ክፍሎችም የክፍትና ነፃ ማኅበረሰብን የአኗኗር ዘዬ ለምደው የኖሩ ሁሉ እንግዲህ በፍተሻና በጥበቃ የታጀበ አዲስ ዓይነት ሕይወት መልመድ ሊኖርባቸው ነው እየተባለ ነው፡፡ ዘገባውን ለማዳመጥ የተያያዘውን የድምጽ ፋይል በመጫን ያዳምጡ።

የዓለም ታላላቅ ከተሞች ፀጥታ ጥበቃቸውን አጠናክረዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:48 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG