በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስንና የኢትዮጵያን የዘመናት ግንኙነት የሚዘክር ዐውደ ርእይ ተከፈተ


የዩናይትድ ስቴትስንና የኢትዮጵያን የዘመናት ግንኙነት የሚዘክር ዐውደ ርእይ ተከፈተ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:49 0:00

ከ120 ዓመታት በፊት፣ በወርኀ ታኅሣሥ 1896 ዓ.ም.፣ እንደ አውሮፓውያኑ 1903፣ ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አሐዱ ብለው የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡

ኢትዮጵያ፣ የጣሊያን ወራሪ ጦርን በዓድዋ ድል ካደረገች ከወራት በኋላ፣ በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቨልት ወደ ኢትዮጵያ የተላኩት ዲፕሎማት ሮበርት ፒ. ስኪነር፣ ከንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ጋራ የንግድ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ይህ ፊርማ፣ ለ120 ዓመታት ለዘለቀው የአገራቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመሪያ ኾኖ ተመዝግቧል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የተጀመረበትን 120ኛ ዓመት በመዘከር ላይ የሚገኘው በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲም፣ ረዥሙን የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪክ የሚያስቃኝ የፎቶ ዐውደ ርእይ አዘጋጅቷል፡፡

የአገራቱን 120ኛ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመዘከር በብሔራዊ ሙዚየም የተዘጋጀውን የፎቶ ዐውደ ርእይ፣ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ እና የቱሪዝም ሚኒስትር ደ'ኤታ ስለሺ ግርማ፣ ትላንት ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጎብኚዎች እይታ መርቀው ከፍተዋል፡፡

አምባሳደር ማሲንጋ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ዐውደ ርእዩ የሁለቱን ሀገራት የረዥም ዓመታት ትብብር እና ትስስር የሚተርክ ስለመኾኑ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት እና ሕዝቦች መካከል ያለውን ዘላቂ ትስስር የሚያሳይ ዐውደ ርእይ፣ መኾኑን የተናገሩት አምባሳደር ኧርቪን “በእነዚኽ፣ በተመረጡ ፎቶግራፎች አማካይነት፣ በሁለቱ አገሮቻችን መካከል በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና እና በኢኮኖሚ ልማት መስክ ያሉ መሠረቶችንና ትስስሮችን እናከብራለን። እያንዳንዱ ምስል ሁለቱን

ማኅበረሰቦቻችንንና ሁለቱን አገሮቻችንን አንድ የሚያደርጓቸውን ጠንካራ፣ ጽኑና የረጅም ጊዜ ትስስርን ለማስታወስ የሚረዳ ነው።” ብለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ደ'ኤታ ስለሺ ግርማ ደግሞ፣ ከሰሃራ በታች ካሉ የአሜሪካ የቅርብ አጋር ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መኾኗን ገልፀው፣ “የኢኮኖሚ ልማት፣ ደኅንነት፣ ጤናንና ትምህርትን ጨምሮ በተለያዩ የትብብር መስኮች በጋራ እንሠራለን፡፡ በባህል እና በሕዝብ ለሕዝብ መስኮች ያለን ግንኙነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ የዛሬው የፎቶ ዐውደ ርእይም፣ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል በዘለቀው የረዥም ጊዜ ግንኙነት ውስጥ ቁልፍ ኹነቶችን የሚያሳዩ ማራኪ ምስሎች የሚታዩበት ነው፡፡” ብለዋል።

በዐውደ ርእዩ፣ ዳግማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ምኒልክ እና ሮበርት ስኪነር፥ የንግድ ስምምነት ከተፈራረሙበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በኹለቱ ሀገራት መካከል ያሉ ዋና ዋና ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችንና ትብብሮችን የሚያሳዩ ምስሎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡

ለስምምነት ፊርማው፣ ስኪነር፥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1903 ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ የተደረገላቸውን አቀባበል፤ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ1954 ኋይት ሐውስን ሲጎበኙ እና ይህን በማድረግም የመጀመሪያው የአፍሪካ መሪ መኾናቸውን፤ ፋሺስት ጣሊያን በኢትዮጵያ ዳግም ወረራ በመፈጸም ያደረሳቸውን በደሎች በመቃወም አሜሪካውያን በኒውዮርክ እና ቺካጎ በ1935 ሰልፍ ማድረጋቸውን፤ በዚኹ ዓመት አፍሪካ አሜሪካዊው ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ከፋሺስት ጣሊያን ጋራ በሚደረገው ውጊያ፣ ኢትዮጵያን ለማገዝ በፈቃደኝነት ከቺካጎ መምጣቱንና የኢትዮጵያ አየር ኀይል መሪ ተደርጎ በውጊያው መሳተፉን የሚያሳዩ ምስሎች በዐውደ ርእዩ ከሚገኙት መካከል ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ተጠባባቂ ምክትል አምባሳደር ናኦሚ ፌሎውስ፣ ዐውደ ርእዩ፥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ከማንጸባረቅ ያለፈ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

አክለውም “ዐውደ ርእዩ በትዕይንቶቹ ለማሳየት ተስፋ ያደረገው፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጥልቅ እና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን ነው፤ የግንኙነቱን ቀጣይነትም እንዲሁ። በብዙ ዘርፎች፣ በተለይ በጤና፣ በግብርና እና በትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ እንተባበራለን። ስለዚህ ለማሳየት እየሞከርን ያለነው፣ ዲፕሎማሲያዊ እና የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነትን ብቻ ሳይኾን፣ ጥልቅ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትንም ነው። ይህ ለሁለቱም ወገኖች የሚጠቅም ግንኙነት ነው፡፡” ብለዋል።

ትላንት ረቡዕ፣ በብሔራዊ ሙዚየም የተከፈተው ይኸው ዐውደ ርእይ፣ እስከ ግንቦት 18 ቀን ለጎብኚዎች ክፍት ኾኖ ይቆያል። በመቀጠልም፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በሃያት ሪጄንሲ ሆቴልም ለእይታ እንደሚቀርብ ተጠባባቂ ምክትል አምባሳደሯ ናኦሚ ፌሎውስ ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG