በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ህጻናትን ከጥቃት ለመጠበቅ የጦር መሳሪያዎች ሕገ ወጥ ፍሰት መቆም አለበት” የተመድ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ተዋናይት ዳናይ ጉሪራ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የሆነችው ተዋናይት ዳናይ ጉሪራ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የሆነችው ተዋናይት ዳናይ ጉሪራ

ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ህጻናትን መድፈር የሚፈልግ ሰው አንድ ዶላር የማይሞላ ገንዘብ ከፍሎ መፈጸም ይችላል፡፡ እንዲህ ያለውን ወንጀል ለመከላከል አንዱ መንገድ በድብቅ የሚተላለፈውን የጦር መሳሪያ ማስቆም ነው” ስትል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የሆነችው ተዋናይት ዳናይ ጉሪራ ዲፕሎማቶችን አሳስባለች፡፡

ዚምባቡዌያዊት አሜሪካዊት ተዋናይ እና ጸሃፊ ተውኔት ዳናይ ጉሪራ ለመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አባላት ባደረገችው ንግግር “በምስራቅ ኮንጎ በሚገኝ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ አንድ ማስቲካ በማይገዛ ገንዘብ፣ የሚደፈር ልጅ ለማግኘት ይቻላል” ብላለች፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ አ አ ባለፈው 2023 ዓ.ም ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች 3ሺህ 688 አስገድዶ የመድፈር ፡ በደቦ የመድፈር እና የጠለፋ አድራጎቶች መፈጸማቸውን አረጋግጠን መዝግበናል ያለ ሲሆን አሃዙ በቀደመው 2022 ዓ.ም ከነበረው በሃምሳ ከመቶ የሚበልጥ መሆኑን አክሎ አመልክቷል፡፡

ሰባ ወይም ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት የመድፈር አእድራጎቶች የተፈጸሙት ትናንሽ እና ቀላል የጦር መሣሪያዎችን በመጠቀም መሆኑን ገልጾ፣ ሰለባዎቹ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ አብዛኞቹ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች በይፋ ስለማይናገሩ የሰለባዎቹ ትክክለኛ ቁጥር ከተጠቀሰው በእጅጉ ሊበልጥ እንደሚችል የመንግሥታቱ ድርጅት ሳይጠቁም አላለፈም።

ተዋናይቱ ቁጣ በተመላበት ንግግሯ በሱዳን፡ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ በኢትዮጲያ ወይም በሄይቲ ጾታዊ ጥቃት ፈጻሚዎች የጦር መሣሪያ ማዕቀቦችን በግልጽ በመጣስ እስከአፍንጫቸው የታጠቁ ናቸው “ ብላለች፡፡ አያይዛም “ዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ አቅርቦት ሰንሰለቱ እየተበጣጠሰ ስለመሆኑ ብዙ ብንሰማም አሁንም መሣሪያ መጉረፉ እንደቀጠለ ነው” ብላለች፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት በጦርነት ቀጣናዎች የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ጉዳይ ልዩ ተወካይ ፕራሚላ ፓተን ለጸጥታ ምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፈው እ አ አ 2023 ዓ.ም በ21 የጦርነት ቀጣናዎች ቢያንስ 58 በሚሆኑ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ሴቶች እና ህጻናት ለመደፈር እና ለሌላም ጾታዊ ጥቃት እንደተጋለጡ አውስተዋል፡፡ አስከትለውም “ እኛው በአቅርቦት ሰንሰለት፣ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ እንዲያገኙ እያደረግን በንግግር ጾታዊ ጥቃት የሚፈጽሙትን ልናወግዝ አይገባም” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG