በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ከእስር ተለቆ ወደ አገሩ ተመለሰ


ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ
ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ

በአዲስ አበባ ለአንድ ሣምንት በእስር ላይ የቆየው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ፣ ዛሬ ሐሙስ ከእስር መለቀቁን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሲፒጄ አስታወቀ።

አፍሪካ ኢንተለጀንስ ለተሰኘ ተቃማጭነቱ በፈረንሳይ የሆነ የዜና ድረ ገጽ ዘጋቢ የሆነው ጋሊንዶ ከእስር እንደተለቀቀ፣ ወዲያው ወደ ፈረንሳይ መመለሱንም የመብት ድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።

ጋሊንዶ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ እና፣ በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ዘገባ ለመሥራት መሆኑን የሚሠራበት የሚዲያ ተቋም እስሩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ መዘገብ የሚያስችለው የጋዜጠኝነት ቪዛ መያዙን እና ከኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን አስፈላጊውን ፈቃድ ማግኘቱንም አመልክቷል።

ጋሊንዶ አዲስ አበባ በሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለው፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ከሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ጋር ቃለ መጠይቅ እያደረገ በነበረበት ወቅት ነው።

የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ "የጋሊንዶ መፈታት ትልቅ ዜና ነው" ማለታቸውን የጠቀሰው የድርጅቱ መግለጫ "ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መታሰሩ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ሞያ አደገኛ መሆኑን ያሳየ ነው" ማለታቸውንም ገልጿል።

ጋሊንዶ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኃላ አብረውት ከታሰሩት አቶ በቴ ጋር ቅዳሜ፣ የካቲት 16፣ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ምድብ ችሎት መቅረባቸውን እና "ከሁለት ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመዲናዋ አመፅ ለመቀስቀስ በማሴር" መከሰሳቸውን የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ አንጀላ ኩዊንታል ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀው ነበር።

ኢትዮጵያ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ማሰሯን ሲፒጄ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:56 0:00

በጋዜጠኛው የሞባይል ስልክ ላይ ምርመራ ለማድረግ እና ተባባሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፖሊስ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ፍርድቤቱ የአንድ ሳምንት የምርመራ ጊዜ የፈቀደ ሲሆን፣ ጋዜጠኛው በነገው ዕለት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶት ነበር።

ስለአፈታቱ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ወዲያውኑ አልተገኘም። "የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም በእስር ያሉ እና በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ለወራት የተሠቃዩ የሚገኙ ሌሎች ስምንት ጋዜጠኞችንም መልቀቅ አለባቸው" ያሉት ሙሞ፣ መንግስት ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ዘገባ መስራት እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው እና ስራቸውን በመስራታቸው የበለቀል እርምጃ እንደማይወሰድባቸው እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

ሲፒጄ ያለፈውን የፈረንጆቹ 2023 ዓ/ም በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ስምንት ጋዜጠኞችን በማሠር፣ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG