በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጎንደር ግጭት ሰው መሞቱን ነዋሪዎች ገለፁ


በጎንደር ግጭት ሰው መሞቱን ነዋሪዎች ገለፁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:48 0:00

በአማራ ክልል በጎንደር ከተማና አካባቢዋ ካለፈው ሣምንት መጨረሻ አንስቶ በፋኖ ታጣቂ ቡድንና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በነበረ ግጭት “ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሲቪሎች ተገድለዋል” ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በከተማዋ ዙሪያ አይባና ፈንቅጥ በተባሉ ቦታዎች በከተማው ውስጥ ደግሞ በተለምዶ ደሣለኝ፣ ኅዳሴና ሸዋ ዳቦ በሚባሉ አካባቢዎች ካለፈው አርብ ጀምሮ ከባድ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

የጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውን የነገሩንና በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ማንነታቸውን እንዳንገልፅ የጠየቁ ሰው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና የፋኖ ታጣቂዎች ካለፈው ሣምንት አርብ ጀምሮ እስከ ትላንት፣ እሁድ ምሽት ድረስ በከተማዪቱ ዙሪያ በሁለት አቅጣጫ ተኩስ መለዋወጣቸውን ጠቅሰዋል።

በኋላም የተኩስ ልውውጡ ወደ ከተማዪቱ ዘልቆ መግባቱንና ሲቪሎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ሸዋ ዳቦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሚኖሩ የገለፁልና በተመሳሳይ ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ ነዋሪም በአካባቢው በነበረው የተኩስ ልውውጥ “ጎረቤቶቼን ጨምሮ ሌሎችም ሲቪሎች ተገድለዋል” ብለዋል።

ደረሰ የተባለውን ጉዳትና መጠኑን ለማረጋገጥ ከፖሊስና ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል መረጃ ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት አልተሳካም።

ካለፈው ሣምንት መጨረሻ ጀምሮ ጎንደር ከተማ ውስጥ በነበረው ግጭት እስካሁን እንቅስቃሴ አለመጀመሩን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

የሰሞኑ ግጭት የተሰማው የገናና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር ዝግጅቶች መደረጋቸው እየተገለፀ ባለበት ወቅት ነው። በተለይ በጎንደር ከተማ በየዓመቱ በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል “አስፈላጊ” ያሉት ዝግጅት መደረጉን የከተማዋ እና የክልሉ አስተዳደር ገልፀዋል።

ሰሞኑን በአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን የተጠቀሱት የአማራ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና የኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እንየው ዘውዴ “በዓላቱን ለማክበር የሚያስችል ሰላም መረጋገጡን” ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በከተሞችና ዙሪያቸው የሚካሄደውን ጨምሮ በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የቀጠለው ግጭት የሠላማዊ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣሉን በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች ሲያሳስብ ቆይቷል።

ኮሚሽኑ ባለፈው ኅዳር ባወጣው መግለጫ “ሰላማዊ ዜጎች፣ ንብረታቸው፣ እንዲሁም የህዝብ መሠረተ ልማትና የአገልግሎት ተቋማት ዒላማ መደረግ የለባቸውም” ሲል በብርቱ አሳስቧል።

የዚህን ዘገባ ዝርዝር ከተያያዘው ፋይል ያድምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG