የግንቦት ሰባት ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሪፖርት እንደደረሰው የእንግሊዝ መንግሥት አስታውቋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መልዕክት “የእንግሊዝ ዜጋ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሰኔ 17 የመን ውስጥ መጥፋታቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእንግሊዝ ባለሥልጣናት ለንደን የሚገኙትን የየመን አምባሣደርን ማነጋገርን ጨምሮ የየመን ባለሥልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ያሉበትን ቦታ እንዲያገኙ ወይም እንዲገልፁልን ጫና ሲያሣድሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን የሚገልፁ ሪፖርቶች የደረሱን በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በአፋጣኝ እንዲያረጋግጡልን ሥጋታችንንም እየገለፅን እንጠይቃለን፡፡ ለቤተሰቦቻቸው የቆንስላ ድጋፍ መስጠታችንን እንቀጥላለን” ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአቶ አንዳርጋቸው ደኅንነት ጉዳይ የሚያሠጋው መሆኑን ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮ በሰጡት መግለጫ “ኢትዮጵያ አቶ አንዳርጋቸውን ዓለምአቀፍ ግዴታዎቿን እንደምታከብር በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንድትይዝ” ጠይቀዋል፡
የሂዩማን ራይትስ ዋችን መግለጫ ለማንበብ ከታች የተያያዘውን ማገናኛ ተጭነው ይከተሉ፡፡
http://www.hrw.org/news/2014/07/07/ethiopia-fears-safety-returned-opposition-leader-0
የመን የሚገኙት የሂዩማን ራይትስ ዋች መርማሪ ቤልኪስ ቬለ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ አቶ አንዳርጋቸው የሚገኙት ኢትዮጵያ ለመሆኑ እርግጠኛ መሆናቸውንና የተላኩትም ሰንዓ አየር ጣቢያ ላይ በተያዙ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መሆኑን ከታማኝ ምንጮች ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡
ግንቦት ሰባት “ሁላችንም አንዳርጋቸው ፅጌዎች ነን” ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
ግንቦት ሰባት ያወጣውን መግለጫ ሙሉ ቃል ለማንበብ ከታች የተቀመጠውን ማገናኛ ተጭነው ይከተሉ፡፡
http://www.ginbot7.org/2014/07/06/ከግንቦት-7:-የፍትህ፣-የነፃነትና-የዲሞክ/
ለቪኦኤ ዘገባ ከላይ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡