በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"የገደሉት ልጄ አስከሬን ላይ ቁጭ በይ ብለው ደበደቡኝ" ደምቢ ዶሎ የተገደለ ወጣት እናት


ደንቢዶሎ
ደንቢዶሎ

በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ ውስጥ ትናንት ማክሰኞ ማምሻው ላይ ከመንግሥት ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ። የአንደኛው ወጣት ወላጅ እናት እኔንም የልጄ አስከሬን ላይ ጥለው ደበደቡኝ ብለዋል።

በመንግሥት ታጣቂ ጥይት ህይወታቸው ያለፈው ሁለቱ ሃይሉ ኤፍሬም እና ኢብሳ ሩንዴ የሚባሉ ሲሆኑ የ16 ዓመቱ ወጣት ሃይሉ ኤፍሬም ከተማዋ ውስጥ ተኩስ በመከፈቱ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ከተኩሱ ለማምለጥ ሲሮጥ መትተው ገደሉት ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

“ደሞቢ ዶሎ መሃል ከተማ ነበር ተኩስ የተጀመረው። ወደ ቀበሌ ዜሮ አምስት አካባቢም ተኩስ ነበር ። ልጆቹን እያባረሩዋቸው ሲመጡ ወጣት ሃይሉ ኤፍሬም በቅጽል ስሙ ቦጌ ነው የሚባለው ቀበሌ ዜሮ ሰባት በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ነው የተገደለው ።” ብለዋል የአሜሪካ ድምፅ ያነጋጋራቸው የከተማዋ ነዋሪ።

ሌላው ወጣት ኢብሳ ሩንዴ ደግሞ ግቢው ውስጥ ቆሞ እንዳለ ተኩሰው ገድለውታል ሲሉ የደምቢ ዶሎ ነዋሪ አስታወቀዋል። አስከሬኑን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ላይ እንዳሉ የመንግሥት ታጣቂዎቹ አስቁመው ወደቤት መልሷቸው ሲሉ ነዋሪው አክለው አመልክተዋል።

ከሟቾቹ መካከል የአስራ ስድስት ዓመቱን ወጣት የሃይሉ ኤፍሬም እናንት ወይዘሮ ታደሉ ተማምን በስልክ አግኝተን የልጃቸውን መገደል ሰምተው እንደሆነ ጠየቅናቸው።

“ ቤት ውስጥ ነበርኩ ። እሱ ደግሞ ከልጆች ጋር ሊጫወት ወጣ ብሎ ነበር። ከተማ ውስጥ ብጥብጥ ተነሳ ሲባል መሯሯጥ ጀመሩ። ከፊት ይሮጥ የነበረውን ልጄን መትተው ጣሉብኝ። ጓደኞቹ መጥተው ሲነግሩኝ ሮጬ ሄድኩ።ስደርስ ልጄ ሜዳ ላይ ተዘርግቷል ። አንድ ያለኝ ተስፋ እሱ ነበር። እንደ አባትም ሆኖ በባሌም ምትክ የቀን ሥራ እየሰራ የሚረዳኝን ልጄን ነው ያጣሁት” ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ጥለውኝ ሲሂዱ ብጮህ ሰዉ ሁሉ ፈርቶ ሸሽቱዋል። እኔና ሴቷ ልጄ ሜዳ ላይ ብቻችንን አለቀስን ያሉት የሟቹ ወጣት እናት አንገቱ ላይ መትተው ነው የገደሉብኝ ብለዋል። በኃላም ጎረቤቶች ተሰብሰበው ረድተውኝ ልጄን ሸኙልኝ። የአስከሬን ሳጥን መግዣ እንኳን አልነበረኝም ብለዋል።

ከቂለም ወለጋ የፖሊስ አዛዥ ምላሽ ለማግኘት ደውለን ነበር። ይሁን እንጂ አዛዡ ኮማንደር ቦደና ስልኩን ካነሱ በኃላ ዘግተውታል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።

"የገደሉት ልጄ አስከሬን ላይ ቁጭ በይ ብለው ደበደቡኝ" ደምቢ ዶሎ የተገደለ ወጣት እናት
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:04 0:00

XS
SM
MD
LG