በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በታይዋን ርዕደ መሬት 7 ሰዎች ሞቱ ከ700 በላይ ቆሰሉ

ታይዋን ምስራቃዊ ግዛት ዛሬ ረቡዕ ማለዳ ከባድ ርዕደ መሬት ደርሶ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ከ700 በላይ ቆስለዋል፡፡ በርዕደት መለኪያው ሪክተር ስኬል 7 ነጥብ 2 ባስመዘገበው የመሬት መናወጥ ከባድ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥም የደረሰ ሲሆን በርካታ ህንጻዎችም ወድቀዋል፡፡ ከታይዋን ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ዘልቆ ተሰምቷል የተባለው ርዕደ መሬት በሀገሪቱ በ25 ዓመታት ከደረሱት ሁሉ ከባዱ ርዕደ መሬት ነው፡፡ በርዕደ መሬቱ በማዕከላዊ ታይዋን አንድ ሕንፃ ሙሉ በሙሉ ሲወድም 15 ህንጻዎች በከፊል ወድመዋል፡፡ ሌሎች 67 የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተለይ ሁዋልያን በተባለቸው የምስራቅ ታይዋን ከተማ ብቻ ቢያንስ 26 ህንጻዎች ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ሲወድቁ ያዘመሙ ህንጻዎችም አሉ፡፡ በማሕበራዊ መገናኛዎች የወጡ ምስሎች ሊወድቅ የደረሰ ህንጻ እንዲሁም በዋና ከተማዪቱ ታይፔይ የተነቃነቁ ህንጻዎች ጨምሮ ከፍተኛ መዋቅራዊ ጉዳት መድረሱን አሳይተዋል፡፡ የነፍስ አድን ሠራተኞች ከህንጻዎች ፍርስራሽ ስር ተቀብረው መውጫ ያጡ ሰዎች ለማትረፍ ሲረባረቡም ታይተዋል፡፡ ተራራማ በሆኑ አውራ ጎዳናዎች ላይ ቁልቁል የተንከባለሉ ቋጥኞች መንገድ በመዝጋታቸው በተፈጠረው የትራፊክ እክል በርካታ ሰዎች መውጫ አጥተዋል፡፡ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በመሬት ርዕደቱ የተበላሹ አውራ ጎዳናዎችና የባቡር ሀዲድ መስመሮችን በመጥረግ እስከ ነገ ሀሙስ ሥራ ለማስመጀር ተስፋ አድርገዋል፡፡ ብዙዎቹ ነዋሪዎች ስለ አደጋው የደረሳቸው ማስጠንቀቂያ ባለመኖሩ በሀገሪቱ የአደጋ ጊዜ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ላይ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በሚቀጥሉት አራት ቀናት ከ6.5 እስከ 7 የሚደርስ ተከታይ ርዕደ መሬት እንደሚኖር ማዕከላዊ የአየር ሁኔታ አስተዳደር አስጠንቅቋል፡፡ በደሴቲቱ የደረሰው ርዕደ መሬት አጎራባቾቹ ጃፓን፣ ፊሊፒንስ እና አንዳንድ የቻይና ክፍሎች ድረስ ዘልቆ የነዘራቸው መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ታይዋንን እ.ኤ.አ. በ 1999 ዓመተ ምሕረት የመታት በሬክተር 7.6 ያስመዘገበ ርዕደ መሬት 2,400 የሚጠጉ ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል።


ተጨማሪ ይጫኑ

XS
SM
MD
LG