በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዜና

አንቶኒዮ ጉቴሬሽ /የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ/ - ማዕከላዊ ማሊ ውስጥ ሞፕቲ ከተማ ውስጥ በተገኙበት ጊዜ፤ ግንቦት 22/2010 ዓ.ም. - ፎቶ - ማማዱ ቦኩም

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ የዓለም ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ምሥረታ ሰባኛ ዓመትን ለማክበር ወደ ማሊ ሄደዋል። ምዕራብ አፍሪካዊቱ ማሊ ሚኑስማ በሚል ምኅፃር የሚጠራው የመንግሥታቱ ድርጅት ኃይል የሚገኝባት ሃገር ስትሆን ተልዕኮውን ለማጠናከር እንደሚሠሩ ዋና ፀሐፊው ቃል ገብተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ የዓለም ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ምሥረታ ሰባኛ ዓመትን ለማክበር ወደ ማሊ ሄደዋል።

ምዕራብ አፍሪካዊቱ ማሊ ሚኑስማ በሚል ምኅፃር የሚጠራው የመንግሥታቱ ድርጅት ኃይል የሚገኝባት ሃገር ስትሆን ተልዕኮውን ለማጠናከር እንደሚሠሩ ዋና ፀሐፊው ቃል ገብተዋል።

በዓለም ዙሪያ ግዳጅ ላይ ሳሉ በተገደሉ የድርጅቱ ወታደሮች ቁጥር እጅግ አቻ የሌለውን ሚኑስማን ይበልጥ ለማጎልበት እንዲቻልም ጉቴሬሽ የድጋፍ ጥሪ አሰምተዋል።

ግንቦት 21 ዓለምአቀፍ የሰማያዊ ቆብ ቀን ተብሎ ይታወቃል። ስለሰላም ቆመው ስለሰላም የወደቁ የዓለም አቃብያነ-ሰላም ወንዶችና ሴቶችን ለማሰብ፣ ጀብዱና ተጋድሏቸውን ለመዘከር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደነገገ ቀን ነው። እናም የዘንድሮውን ዕለት ለማክበር ጠቅላይ ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ባማኮ የገቡ ጊዜ የመንግሥታቱ ድርጅት ቤተሰብ በመላ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ተቀበላቸው።

ማሊ የዓለም ልዑካን የነበሩ 172 ሰዎች የተገደሉባት ሃገር ነች። መቶው ባለ ሰማያዊ ቆብ ወታደሮች ነበሩ። የመንግሥታቱ ድርጅት ከተሠማራበት ሁሉ እንዲህ ዓይነት የበረታ ጉዳት በየትኛውም የምድር ጠርዝ አልደረሰበትም።

ማሊ 13 ሺህ አምስት መቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወታደሮችን ለግዳጅ ተቀብላለች። በተጨማሪ ፈረንሣይ ለባርኻኔ ዘመቻዋ ያሰማራቻቸው ወታደሮች አሏት። የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ የማሊን ወታደሮችና አጋዥ ክፍሎች ያሠለጥናል። ቡድን አምስት ወይም ጂ ፋይቭ ተብለው የሚጠሩት ማሊ፣ ኒዠር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቻድና ሞሪታኒያ ደግሞ የራሣቸው የአካባቢው ፀጥታ አስከባሪ ኃይል አላቸው።

ማሊ እምብርት ላይ የሚገኘውን የጂ ፋይቭ ጠቅላይ ዕዝ ለመጎብኘት አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ከትናንት በስተያ ጎራ ብለው ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጉብኝታቸውን ባጠናቀቁ ጊዜ ለጂ ፋይቭ የፈጠነ ዓለምአቀፍ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደርስ ጠይቀዋል። የድርጅታቸው ኃይል የተሰጠው ግዳጅ ሳህል አውራጃ ውስጥ ሽብርተኛ ንቅናቄዎችንና የተደራጀ ወንጀልን መዋጋት እንዲሁም ሲቪሉን ሕዝብ ከጥቃት መጠበቅ መሆኑን ለጋዜጠኞች የተናገሩት ጉቴሬሽ የኪሣቸው ነገር ግን በጣም አንገራጋሪ እንደሆነም አሳብቀዋል።

የማሊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሜሉ ቡቤዬ ማይጋ ናቸው ጦራቸውን እየጎበኙ ሳሉ የክብር ዘቡ ሠላምታ የሚሰጣቸው።

ምንም እንኳ የማሊ የራሷ ወታደሮች ሠፈሩን ለማተራመስ ይንቀሳቀሳሉ ከሚባሉ ኃይሎች ጋር እየተዋጉ ቢሆንም የተሻለ ትጥቅ፣ ረቀቅ ያለ መሣሪያ ጠርቀም ያለ ደመወዝ ሊደርሱላቸው ይገባል። እስከዚያው ግን ማሊ ዳር ድንበሯን ለማስከበር፣ ሕዝቧንም ለመጠበቅ አጋዥ የሆኑት የውጭ ኃይሎች ጫማ እየረገጣት ይቆያል።

እነዚያ ባዕዳን ጦሮች ታዲያ በተለይ ደግሞ የመንግሥታቱ ድርጅት የማሊ ልዑካን የራሣቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች እያጠናከሩ እንደሚቀጥሉ ጉቴሬሽ አስታውቀዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የማሊ ተልዕኮ ሚኑስማ የሠፈረበት የቲምቡክቱ አየር ጣቢያ ባለፈው ሚያዝያ ውስጥ ድንገት በተከፈተበት አስደንጋጭ ጥቃት መመታቱ ወታደሮቹ ምን ያህል ለአደጋ የተጋለጡ እንደሆነ ማስታወሻ ሰጥቶናል ብለዋል አንቶኒዮ ጉቴሬሽ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባማኮ ውስጥ ጥብቅ የሆነ የቅኝት ሥርዓቶችን እንደሚዘረጋ፣ የተራቀቁ የማስጠንቀቂያ መዋቅሮችንና በሃገሪቱ ሰሜን በሚገኙ አንዳንድ የጦር ሠፈሮች ውስጥ ራዳሮች እንደሚተከሉ፤ ቦምቦችንና የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማደንም አነፍናፊ ውሾች እንደሚሠማሩ፤ የአካባቢ ቅኝትና የአደጋ ማስጠንቀቂያ የተጠናከሩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ የተናገሩት ጉቴሬሽ ተራራ ሸንተረሩን ለመጠበቅና ተቆጣጥሮ ለመቆየት የሚያስችሉ በርካታ ዘመቻዎች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል።

እና ይህ በቂ ይሆናል? ብዙው እንግዲህ የሚወሰነው ለማሊ፣ ለሚኑስማ እና ለጂ ፋይቭ የሳህል ኃይል ከዓለምአቀፉ ድጋፍ ከሚገኘው የገንዘብ መጠን ይሆናል።

አሁን ግን እጅግ የከፋው የካዝና መመናመን ለወደፊቱ የከበዱ ችግሮችን የደገሠ ነው። “ማሊ ብትወድቅና ብትሰበር፤ ስብርባሪዋና ፍንጥርጣሪዋ መከራን የሚዘራው ለማሊ ጎረቤቶች ብቻ ሳይሆን - አሉ ጉቴሬሽ፤ መዘዙ ከሳህል እስከ መላ ሜዲቴራኒያን ክልልና ዘልቆም ወደ አውሮፓ ጠልቆ የሚጎዳ ይሆናል።”

ሽብር ፈጠራ ሽብር ፈጥሮ በግርግሩ ውስጥ ከመተራመስ ይልቅ የሽብርተኝነትን ችግር ከፅንሱ መከላከል ይበጃል - ሲሉ መክረዋል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የ“ሰማያዊ ቆብ ቀን” የተከበረው አፍሪካ ውስጥ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:27 0:00

በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ በመንግሥት በተጠራ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ ለተገኙ ተሣታፊዎች ይከፈላል ከተባለ የውሎ አበል ክፍያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ አለመግባባት ወደ ፖሊስና ወጣቶች ግጭት አምርቶ በአንድ ወጣት ላይ ከባድ ድብደባ እንደፈፀመ፤ በሁለት የፖሊስ አባላት ላይም ጉዳት እንደደረሰ ታውቋል።

ከግንቦት 19 እስከ ግንቦት 21 በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሲደረግ የውሎ አበል እንደሚከፈላቸው ተነግሯቸው እንደነበርና በስብሰባው የመጨረሻ ቀን በቀን 26 ብር እንደሚከፈላቸው የተገለፀላቸው መሆኑን ወጣቶቹ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የተነገራቸቸው የአበል መጠን የቀን ሥራ ሠርተው ከሚያገኙት በእጅጉ ያነሰ መሆኑን በማመልከት ስብሰባው ላይ ለነበሩት ከንቲባ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ምንም አይነት ሥራ እንደሌለውና በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት የተናገረው ወጣት ዮሃንስ ገብረኪዳን ስለ ሁኔታው ሲያብራራ “800 የሚሆን ተሳታፊ ነበር። ሰዉ የውሎ አበል አለ ብሎ ሲሰበሰብ ከቆየ በኋላ ስብሰባው በሦስተኛው ቀን ሲጠናቀቅ የውሎ አበሉን መጠን አሳውቁን ብሎ ጠየቀ። በቀን 26 ብር ነው እሚከፈላችሁ አሉን። ሥራ አጥ ብላችሁ ከሰበሰባችሁን በኋላ የቀን ሥራ ሰርተን ከ80 ብር እስከ 100 ብር የምናገኝበትን ጊዜያችንን አባከናችሁብን እያሉ ከንቲባውን መልስልን እያሉ ማናገር ጀመሩ። እሱም ለማረጋጋት እየሞከረ ሳለ አብረውት የነበሩት ጥለውት ሄዱ። በዚህ ጊዜ ነበር ፖሊሶች የመጡትና ወጣቱም ድንጋይ መወርወር የጀመረው” ብሏል።

ፖሊስ ዱላ ሲጀምር ወጣቱም ወደ ሽሽት እንደገባ፤ እርሱም በቅርቡ ወዳገኘው ቤት እንደገባ፤ ያኔ የፖሊስ አባላት ከቤት አውጥተው ነፍሱን እስኪስት እንደደበደቡት ተናግሯል።

“ከቤት አውጥተው መንገድ ላይ ዘረጉኝ። አራት ጊዜ ራሴ ላይ መቱኝ፤ ከዚያ ማጅራቴን በዱላ ሲመቱኝ አዕምሮየን ስቼ ወደቅኩኝ። ሰዉ ተዉ እያላቸ እያገላበጡ መቱኝ። ራሴን ስቼ ስለነበር በፖሊስ መኪና ጭነው ወደ ጣቢያ ወስደው ውጭ ጣሉኝ። ደሜ እየፈሰሰ ከቆየሁ ብኋላ በሰንሰለት አስረው ወደ ሆስፖታል ወሰዱኝ” ብሏል ወጣት ዮሃንስ።

ከአንገቱ በታች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የገለፀው ዮሃንስ ከሆስፒታል ወደ እሥር ቤት እንደመለሱትና በመጨረሻ በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንደለቀቁት ተናግሯል። ሌሎች 13 ወጣቶች እንደታሰሩም ገልጿል።

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘሥላሴ ዘረአውሩክ የተፈጠረው አለመግባባት ከስብሰባው አጀንዳ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለውና ስብሰባው በመግባባት ማለቁን አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ በመንግሥት የፋይናንስ አሠራር የከተማ የቀን አበል ስለማይከፈል ክፍያው የቀን አበል ሳይሆን የሻይ እንደነበር ገልፀው ሆኖም ግን ይኸው ቀድሞ ሊነገራቸው ይገባ እንደነበረ አምነዋል። ስለሆነም “የወጣቶቹ ጥያቄ ተገቢ ነበር፤ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱ የኛ ነው” ብለዋል።

ተፈፀመ የተባለውን ድብደባና እሥራት አስመልክቶ ድንጋይ መወርወርና ሌሎችም አላስፈላጊ አድራጎቶች በወጣቶቹ ተፈፅሟል ያሉት የአድዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ ፖሊስ ሥርዓት ለማስከበር የወሰደው እርምጃ ከመጠን በላይ መሆኑን አለመሆኑን ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

በወጣት ዮሃንስ ላይ የተፈፀመውን ድብደባ እንደሚያውቁና ወደ ህክምና የተወሰደው በፀጥታ አስከባሪዎቹ መሆኑን፤ ግጭቱ ወቅት በሁለት የፀጥታ ጥበቃ አባላት ላይ በድንጋይ ጉዳት እንደደረሰ ከንቲባው አመልክተዋል።

“የተወሰደው እርምጃ ከመጠን በላይ ነው ወይ? ለሚለው ወጣቱ ራሱ ምስክር ነው። ወጣቱ ቆሞ እያለ ወይም ተይዞ እያለ ወይም ደግሞ ምንም ሳያደርግ እንዲህ ዓይነት በደል ተፈፅሞበት ከሆነ በህግም የሚያስጠይቅ ስለሆነ አጣርተን ከመጠን በላይ የሆነ እርምጃ የወሰደው አካል ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ አለበት በሚለው እኔም እስማማለሁ” ብለዋል ከንቲባው።

የታሠሩትን ቁጥር አስመልክቶ በማኅበራዊ መገናኛ እንደተሠራጨው 13 ሳይሆኑ ሰባት እንደነበሩና ከአንድ ቀን በኋላ በዋስ እንደተለቀቁ ከንቲባ ዘሥላሴ ዘረአውሩክ ገልፀው አበሉም 26 ብር ሳይሆን ለሦስቱ ቀናት በድምሩ አንድ መቶ ብር እንደተከፈላቸው ለቪኦኤ ገልፀዋል።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

አድዋ ላይ በፖሊስና በወጣቶች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:39 0:00

ተጨማሪ ይጫኑ

XS
SM
MD
LG