በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዜና

የዩናይትድ ስቴይትስ ጦር ወደ ሊቢያ ተጠግቷል

በሊቢያ የጸረ-መንግስት ተቃውሞ የሚያካሂዱ ቡድኖች የመንግስቱ ታጣቂዎች የዛዊያ ከተማን ለማስለቀቅ ያደረጉትን ጥረት መመከታቸውን አስታወቁ።

ለ42 አመት ሊቢያን ያስተዳደረው የሞማር ጋዳፊ መንግስት በቋፍ ላይ ባለበት ወቅት፤ በነዳጅ ዘይት ሀብቷ የምትታወቀውንና ጠንካራ ይዞታው የነበረችውን የዛዊያ ከተማ በጦር ከቦ ይገኛል።

ተቃዋሚዎቹ ለቪኦኤ እንደገለጹት የአፍቃሪ ጋዳፊ ሀይሎች በታንክ ታጅበው ከተማዋን ዛሬ ማለዳ ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት፤ በጸረ-መንግስቱ ሃይሎች ተመክቶ እንዲያፈገፍጉ ተገደዋል።

ለሰዓታት በዘለቀው ውጊያ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። ተቃዋሚዎቹ ጥቂት መሳሪያ ስላላቸው፤ ብቻቸውን የጋዳፊን መንግስት ለመውጋት እንደማይችሉ ነው የሚናገሩት።

በተቃዋሚዎች እጅ በወደቀችው ምስራታ ከተማ ደግሞ፤ የአይን እማኞች የመንግስቱ ታማኞች ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጁ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከጋዳፊ ሰራዊት እየከዱ ህዝባዊ እንቅስቃሴውን የተቀላቀሉ ወታደሮች የመከላከልና ሌሎች ከተሞችን ነጻ የማውጣቱን ሂደት በመምራት ላይ ናቸው።

በስተምስራቅ ደግሞ የሊቢያ የጦር አውሮፕላኖች የቤንጋዚ ከተማን በቦምብ ለመደብደብ እንደሞከሩ የአይን ምስክሮች ተናግረዋል። ጥረቶቹ በአየር መቃወሚያ ጥይቶች እንደከሸፉ ተቃዋሚዎች አስታውቀዋል። አውሮፕላኖቹ ተመልሰው የጦር መሳሪያ ማከማቻ የሆነችውን የአጅዳቢያን ደብድበዋል።

ሞመር ጋዳፊ ከአሜሪካው ABC ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የአየር ሀይላቸው የጸረ-መንግስት ተቃዋሚዎችን ደብድቧል የሚባለው ከእውነት የራቀ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የምእራባዊያን መንግስታት ጋዳፊ ከስልጣን እንዲወርዱ የቀረበውን ጥሪ “በሳቅ” አፊዘው አልፈውታል። “ህዝቤ ይወደኛል…ለኔ ሲል ይሞታል” ብለዋል ጋዳፊ።

በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴይትስ አምባሳደር ሱዛን ራይስ ሚስተር ጋዳፊ መሳቃቸው ከሂኔታው የራቁና፤ ነገሩ ያልገባቸው መሆናቸውን ያሳያል፤ በዚህ ምክንያት አገር መምራት እንደማይችሉ በዚህና በሌሎች አጋጣሚዎች አሳይተዋል ብለዋል።

የአለም መሪዎች ሞመር ጋዳፊ ከስልጣን እንዲወርዱ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ናቸው።

እንግሊዝ፣ ዩናይትድ ስቴይትስ፣ ጀርመን፣አውስትራሊያን ሌሎች የአውሮፓ ህብረት አገሮች የጋዳፊ ቤተሰብ ያለውን ሀብት እንዳይንቀሳቀስ እንደሚያደርጉ ተስማምተዋል።

በዛሬውለት በዩናይትድ ስቴይትስ የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፤ የጋዳፊ ሀይሎች በህዝባቸው ላይ አፈሙዛቸውን እስኪያነሱ ድረስ መንግስታቸው “ማንኛውንም አማራጭ” ይጠቀማል ብለዋል።

ሚስስ ክሊንተን፤ ሞመር ጋዳፊ ከስልጣን እንዲወርዱ በአጽንዖት ጠይቀዋል። ምርጫው አሉ ሚስስ ክሊንተን ሊቢያን የምታብብ ዴሞራሲያዊት አገር የማድረግና ወደማያልቅ የእርስ-በርስ ጦርነት መዝፈቅ ነው ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴይትስ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሊቢያን ትመርጣለች፤ ሊቢያዊያንም የሚፈልጉት ይሄንን ነው ብለዋል ሚስስ ክሊንተን።

የጸጥታ ሁኔታው እየባሰ በመምጣቱ የዩናይትድ ስቴይትስ ጦር፤ ባህርና አየር ሀይል ሁኔታውን በቅርበት ለመከታተል ወደ ሊቢያ መጠጋቱን ዋሽንግተን ትናንት አስታውቃለች።

ግብጽና ሱዳን የአባይ ወንዝን 98ከመቶ ውሃ ተጠቃሚ ናቸው

የናይል ተፋሰስ አገሮች በአባይ ወንዝ ላይ የሚኖራቸውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተፈረመውን ስምምነት ቡሩንዲ ስድስተኛ አገር በመሆን ተቀላቀለች።

በ1922ዓም በተፈረመው የአባይ ወንዝ አጠቃቀም ስምምነት ላይ ግብጽና ሱዳን 98ከመቶ የሚሆነውን የአባይ ውሃ በጥቅም ላይ እንዲያውሉ ይፈቅዳል።

የአባይ ተፋሰስ አገሮች የውሃው አጠቃቀም ፍትሃዊ እንዲሆን በመጠየቅ፤ በአንድነት የግብጽን መንግስት ጫና ለመቋቋም ነው ስምምነት በመፈራረም ላይ ያሉት።

ይሄንን ስምምነት ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ዩጋንዳ አስቀድመው የፈረሙት ሲሆን፤ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በጽንሰ-ሀሳቡ ተስማምታ ፊርማዋን እንደምታኖር ቃል ገብታለች።

ተጨማሪ ይጫኑ

XS
SM
MD
LG