በሆሮጉድሩ ወለጋ 42 ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸው ፖሊስ አረጋገጠ

ሆሮጉድሩ ወለጋ

  • ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመ ጥቃት መሆኑን ከጥቃቱ የተረፉ ተናግረዋል

በኦሮሚያ ክልል በሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከቅዳሜ የካቲት 27/2013 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ቀናት ማንነትን መሰረት አድርጎ በደረሰባቸው ጥቃት ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ “ኦነግ ሸኔ የተባሉ ታጣቂዎች” የአማራ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችን እየለዩ ጥቃት ማድረሳቸውን ገልፀዋል። ሕይወታቸው ካለፉ ሰዎች በተጨማሪ ቆስለው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ በርካቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎችም ቢሆኑ በአሁኑ ሰዓት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አሉበት ወደተባሉበት ቀበሌዎች በእግራቸው እየሸሹ መሆኑን ገልፀው፤ “መንግሥት ሕይወታችንን ይታደግልን” ሲሉ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የኮምኒኬሽን እና ሚዲያ ኃላፊ ጌታቸው ኢታና ፤ ጥቃቱ መድረሱን ገልፀው እስካሁን ባላቸው መረጃ 42 ሰዎች በኦነግ ሸኔ መገደላቸውንአረጋግጧል።

ጃልመሮ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የምዕራብ ኦሮሚያ አዛዥ ኩምሳ ድሪባ፤እርሱ የሚመራው ጦር ማንነትን፣ ዘርን እና ኃይማኖትን መሠረት አድርጎ ጥቃት እንደማይፈፅም ገልፆየአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ናቸው ብሏል።

ከጥቃቱ የተረፉና ቤተሰቦቻቸው በጥቃቱ እንዳጡ የሚናገሩ ቤተሰቦች ግን የጦር መሳሪያ በሚገባ የታጠቁና የኦነግ ሸኔ መለያ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች እንዳጠቋቸው ገልፀዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ “ኦነግ ሸኔ ጥቃቱን ከፈፀመ በኋላ ሁሌም የሚያሳብብበት አካል ይፈጥራል” ብሏል።

(ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

Your browser doesn’t support HTML5

በሆሮጉድሩ ወለጋ 42 ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸው ፖሊስ አረጋገጠ