ዩክሬይን ለ30 ቀናት ተኩስ እንዲቆም በቀረበው ሐሳብ እንደምትስማማ ትላንት ይፋ ማድረጓን የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት በደስታ ተቀበሉት፡፡ ቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበር የነበሩት ሪፐብሊካኑ ማይክል መኮል "ስምምነት ላይ መደረሱ በጣም አበረታቶኛል፡፡ አሁን ፕሬዚደንቱ የተያዘውን የስለላ መረጃ እና የጦር መሣሪያ ለመልቀቅ የወሰኑ ይመስለኛል፡፡ በጣም ትልቅ ክንዋኔ ነው" ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ እና የዩክሬይን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በኋይት ሐውስ ኦቫል ኦፊስ የተካረረ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬይን የምትሰጠውን የጦር መሣሪያ ርዳታ እና የስለላ መረጃዎች ማጋራቷን እንደምታቋርጥ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀች ይታወሳል። ኾኖም በቀናት የተገደበው የተኩስ ማቆም ስምምነት ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ ከዩክሬይን ጋራ መተባበሯን እንደምትቀጥል ትላንት አስታውቃለች፡፡
ዲሞክራቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ጄሰን ክሮው በበኩላቸው "መጀመሪያም ቢሆን ለነጻነት፣ ለዲሞክራሲ እና ለብሔራዊ ጸጥታቸው የሚዋጉ ዩክሬይናውያንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥለው ድጋፍ የማቋረጥ ርምጃ መወሰድ አልነበረበትም፡፡ ስለዚህ አሁን አስተዳደሩ እገዳውን ማንሳቱ አዎንታዊ ርምጃ ነው" ብለዋል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩክሪይን ሊፈራረሙ የነበረው የዩክሬይን ውድ ማዕድናት ውል ሁለቱ መሪዎች በይፋ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ሳይፈረም መቅረቱ ይታወሳል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ማይክል መኮል " ከዚህ በኋላ እንግዲህ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ወደ ኦቫል ኦፊስ ተመልሰው ይመጡና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነቱ ይፈረማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚያ ደግሞ ጉዳዩ በሙሉ ወደሚስተር ፑቲን ይዞራል" ብለዋል፡፡
ሩሲያ በተኩስ አቁም ዕቅዱ አልተስማማችም፡፡ ፕሬዝደንት ትረምፕ በጉዳዩ ላይ የሚወያዩ ተወካዮች ወደሞስኮ መላካቸውን ትላንት አስታውቀዋል፡፡
መድረክ / ፎረም