በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ያወደመውን እና እስካሁን 10 የሚደርሱ ሰዎችን የገደለውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ሠራተኞች ዛሬ ለአራተኛ ተከታታይ ቀን እሳቱን ለማጥፋት ብርቱ ግብግባቸውን ቀጥለዋል። ለጊዜው ፍጥነቱን ቀንሶ የሚነፍሰው ነፋስ የከሰተውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ውሃ የሚረጩ ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ እስከማለዳው ድረስ ለሊቱንም ሳያቋርጡ መቀጠላቸው ተዘግቧል።
ከትላንት ጀምሮ እየቀነሰ የመጣው ቃጠሎ ይበልጥ በቁጥጥር ሥር ሲውል እና የእሳት አደጋ ሠራተኞች ፍርስራሹን ለማንሳት የሚችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ‘የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም ሊጨምር ይችል ይሆናል’ ሲሉ ባለስልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሰደድ እሳቱን ለመከላከል የሚወሰደውን የፌደራል መንግሥቱን ምላሽ አስመልክቶ ዛሬ አርብ የሚመለከታቸውን ከፍተኛ ባለስልጣናታቸውን ሰብስበው እንደሚያነጋግሩ ዋይት ሀውስ ገልጧል።
በሌላ በኩል ባይደን ትላንት ሐሙስ ከቀትር በኋላ በሰጡት አስተያየት “በሎስ አንጀለስ የደረሰው ከመቼውም የከፋ ቃጠሎ” ሲሉ የገለጹትን ሰደድ እሳት ለመዋጋት የሚያስፈልገው የፌደራል መንግሥቱ አቅም እና ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለካሊፎርኒያ መመደቡን አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ‘ገንዘቡ ለተጎጂዎች ለ180 ቀናት ለጊዜያዊ መጠለያ፣ አደጋ የሚያስከትሉ ነገሮችን ከአካባቢው ለማስወገድ፣ ለፈጥኖ ደራሽ ሠራተኞች ደሞዝ እና ህይወትን ለመጠበቅ የሚያግዙ ወጪዎች በሙሉ ለመሸፈን ይውላል’ ብለዋል።
በተያያዘ ሌላ ዜና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት በኤክስ ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት ‘እጅግ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰ ያለው የሎስ አንጀለሱ ሰደድ እሳት በሰው ሕይወት፣ የብዙ ሺዎች መፈናቀል፣ እንዲሁም በንብረት እና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ያደረሰው ብርቱ ጉዳት ክፉኛ ያሳዘነው መሆኑን ገልጿል።
መድረክ / ፎረም