በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማርገብ፣ የዩናይትድ ስቴትስ አሸማጋዮች የ60 ቀናት ተኩስ ማቆምም ስምምነት ለማስጀመር እየጣሩ መሆኑን ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሮይተርስ አስታወቁ።
ስለድርድሩ ገለጻ የተደረገላቸው አንድ ግለሰብ እና በሊባኖስ የሚሠሩ አንድ ከፍተኛ ዲፕሎማት እንዳመለከቱት፣ ለሁለት ወራት የሚቆየው የተኩስ ማቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ እ.አ.አ በ2006 ደቡባዊ ሊባኖስን ከጦር መሳሪያ ነፃ ለማድረግ ያሳለፈውን '1701' የተሰኘ የውሳኔ ሐሳብ ተግብራዊ ለማድረግ ይጠቅማል ብለዋል።
በቤይሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሳማ ሐቢብ ስለ ውሳኔ ሐሳቡ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "የውሳኔ ሐሳብ 1701ን ተግባራዊ የሚያደርግ እና የእስራኤል እና የሊባኖስ ዜጎችን ወደየቤታቸው የሚመልስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንፈልጋለን" ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተጀመረው እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገው ዘመቻ እየሰፋ ባለበት ወቅት ሲሆን ለሦስት ተከታታይ ቀናት ደቡባዊ የሊባኖስ ከተማ በሆነችው ኪያም አቅራቢያ ከፍተኛ ውጊያ መደረጉን ሂዝቦላህ አስታውቋል።
በአዲሱ የተኩስ አቁም ሀሳብ ላይ እየሰሩ ያሉት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ አሞስ ሆችስቴይን በዚህ ወር መጀመሪያ ቤይሩት ለሚገኙ ጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፣ እስራኤልም ሆነች ሊባኖስ የፀጥታ ምክርቤቱን የውሳኔ ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው የተሻሉ የማስፈጸሚያ ዘዴዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረው ነበር።
መድረክ / ፎረም