በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ ከአውሮፓ በሚገቡ የአልኮል መጠጦች ላይ ከበድ ያለ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታወቁ


የሻምፓኝ እና ወይን መጠጦች ሱቅ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ እአአ መጋቢት 13/2025
የሻምፓኝ እና ወይን መጠጦች ሱቅ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ እአአ መጋቢት 13/2025

የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ በሚገባው ዊስኪ ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ መጣሉን ተከትሎ፣ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ከአውሮፓ በሚገባው የወይን ጠጅ፣ ሻምፓኝና ሌሎች የአልኮል መጠጦች ላይ የ200 በመቶ ታሪፍ እንደሚጭኑ አስጠንቅቀዋል።

የ27 ሃገራት ስብስብ የሆነውን የአውሮፓ ኅብረት "በዓለም የከፋው ታክስና ታሪፍ ጣይ" ሲሉ የገለጹት ትረምፕ፣ "እ.አ.አ በ1993 ሲመሠረት ዓላማው "ከአሜሪካ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት ነው" ብለዋል።

ባለፈው አንድ ወር ከአሜሪካ ከፍተኛ የንግድ ሸሪኮች፣ ማለትም ከሜክሲኮ፣ ካናዳ፣ ቻይናና የአውሮፓ ኅብረት ጋራ የታሪፍ ውዝገብ ውስጥ የገቡት ትረምፕ፣ ታሪፉን መጣሉ አስፈላጊ የሆነው ሃገራቱ ወደ አሜሪካ የሚገባውን አደገኛ ዕጽ እና መድሃኒት እንዲያስቆሙና እንዲሁም የሸቀጥ አምራቾች በውጪ ያላቸውን ፋብሪካ ዘግተው ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ለማስገደድ መሆኑን ይገልጻሉ።

ትረምፕ ትላንት ረቡዕ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ብረታብረት ወደ አሜሪካ በሚልኩ 35 ሃገራት ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል። አውርፓውያኑ በአጸፋው ከአሜሪካ በሚላከው የ28 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጥ ላይ ታሪፍ ጥለዋል። ካናዳ በበኩሏ 20.7 ቢሊዮን ዶላር በሚጠጋ የአሜሪካ ሸቀጥ ላይ ታሪፍ ጥላለች፡፡

አውሮፓውያኑ የሚጥሉት ታሪፍ ያተኮረው እንደ ትረምፕ ባሉ ሪፐብሊካኖች ቁጥጥር ሥር ካሉ ግዛቶች በሚላኩ ሸቀጦች ላይ ነው። ከካንሳስ እና ኔብራስካ በሚላከው ሥጋና ዶሮ፣ ከአላባማ እና ጆርጂያ በሚላከው የእንጨት ውጤት፣ እንዲሁም ከኬንተኪ እና ቴነሲ በሚላከው የአልኮል መጠጥ ላይ ነው። በብረት እና አሉምነም ላይ አንዱ በሌላው ላይ በሚጥለው ታሪፍና ውዝግብ መሃል የአልኮል አምራቾችም ሰለባ ሆነዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ለአሜሪካ ዊስኪ ትልቁ ገበያዋ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የነበረው ታሪፍ መነሳቱን ተከትሎ ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ አውሮፓ የሚላከው የአሜሪካ ዊስኪ በ60 በመቶ ጨምሮ ነበር።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG