ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እንደሆኑ በሚጠረጠሩ ግለሰቦች በአንድ ቤት ውስጥ ታግተው የነበሩ 26 ኢትዮጵያንን እርቃናቸውን ማግኘቱን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ዛሬ ዓርብ አስታውቋል።
ፍልሰተኞቹን ከታገቱበት ከማዳኑ በፊት 30 የሚሆኑት በተሰበረ መስኮት ሾልከው ሳያመልጡ እንዳልቀረ የገለፀው ፖሊስ፣ በአካባቢው ተደብቀው ሊሆን እንደሚችልም አስታውቋል።
በተደረገው ቅድመ ማጣራት 26ቱ ኢትዮጵያውያን ሳንድሪንጋሃም በተሰኘ ከጆሃንስበርግ በስተ ሰሜን ከሚገኝ መንደር መኖሪያ ቤት ውስጥ ራቁታቸውን ካለ ሰነድ ታግተው እንደነበር ፖሊስ ገልጿል። የተሰበረ መስኮትና አጥር የተመለከቱ ነዋሪዎች ትላንት ሐሙስ ምሽት ላይ ለፖሊስ መጠቆማቸው ተመልክቷል።
በጥቆማው መሠረት የተንቀሳቀሰው ፖሊስ 15ቱን እርቃናቸውን እንደሆኑ ሲያገኝ፣ 11 የሚሆኑት ደግሞ ለማምለጥ ሲሞክሩ ሰውነታቸው በመቁሰሉ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። በአጠቃላይ በቤቱ ውስጥ ተይዘው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች 60 እንደሚሆኑ የገመተው ፖሊስ፣ ታግተው የቆዩት ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ለጊዜው እንደማይታወቅም ገልጿል።
ሦስት የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በሕገ ወጥ አዘዋዋሪነት ተጠርጥረው መያዛቸውንም ፖሊስ አስታውቋል።
ባለፈው ነሐሴ በዚያው አካባቢ 80 ኢትዮጵያውያን ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ካለ በቂ ምግብና የንጽሕና ሁኔታ በአንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ማግኘቱን ፖሊስ አስታውሷል።
በአፍሪካ በኢንዱስትሪ የበለጸገችው ደቡብ አፍሪካ፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሃገራቸውን ለቀው ለሚወጡ ፍልሰተኞች መስህብ ናት፡፡
መድረክ / ፎረም