የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ "ኤኮዋስ" የቀጠናው የጦር ኃይል በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የጸጥታ ተንታኞች ርምጃውን ያደነቁ ቢሆንም፣ የተቋሙ ሦስት አባል ሀገራት በቅርቡ መውጣታቸው ውጤታማነቱን አጠራጣሪ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
የናይጄሪያ መከላከያ ሚኒስትር ሞሃመድ ባዳሩ አቡባካር የኤኮዋስ የጦር ኃይል በተጠንቀቅ ላይ እንደሚሆን ያስታወቁት፣ ትላንት ማክሰኞ በተካሄደው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጥምረት የሆነው ኤኮዋስ 43ኛ መደበኛ የፀጥታ ስብሰባ ወቅት ነው።
5 ሺሕ ወታደሮች እንደሚኖሩት የሚጠበቀው የጦር ኃይል፣ በቀጠናው የሚካሄዱትን ሽብርተኝነት እና ድንበር ዘለል ወንጀሎች ለመከላከል የሚደረግ ቀጠናዊ የፀጥታ እንቅስቃሴ አካል ነው።
አቡበከር በንግግራቸው "ይህ ኃይል በተጠንቀቅ እንዲቆም ሆኖ ሥራ መጀመሩ፣ የሽብርተኝነትን መስፋፋት ለመጋፈጥ እና የዜጎቻችንን ደኅንነት ለማረጋገጥ ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት ያሳያል" ብለዋል።
በተጨማሪ የኤኮዋስ የፀጥታ ኃላፊዎች በጊኒ ባህረ ሰላጤ የባህር ላይ ደኅንነት እና የሰላም ድጋፍ ለማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይም ተወያይተዋል።
የምዕራብ አፍሪካው ተቋም አካል የነበሩት ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር ከኤኮዋስ ተገንጥለው "የሳህል አገሮች ጥምረት" የተባለ ኮንፌዴሬሽን አቋቁመዋል። ወታደራዊ አመራር ያላቸው ሦስቱም ሀገራት፣ ኤኮዋስን " የአባል ሀገራቱን ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የውጭ ሀገራት ጥቅም ማስፈፀሚያ ሆኗል" ሲሉ ይከሳሉ።
መድረክ / ፎረም