በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ የተከሠተውን ድርቅ ተከትሎ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ 109ሺሕ ሰዎች ውስጥ እስከ አሁን ማድረስ የተቻለው ለ27ሺሕዎቹ ብቻ እንደኾነ፣ የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በወረዳው ከ16ሺሕ ኩንታል በላይ የርዳታ እህል እንደሚያስፈልግ ለመንግሥትም ኾነ ለረጂ ድርጅቶች ማሳወቃቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ያስታወሱት የጽሕፈት ቤቱ ሓላፊ አቶ ዓለሙ ይመር፣ እስከ አሁን በመንግሥት በኩል ወደ ስፍራው የተላከው ግን አራት ሺሕ ኩንታል ብቻ እንደኾነና ከሌሎች ረጂ ድርጅቶች የተገኘው ደግሞ 1ሺሕ500 ኩንታል ብቻ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚኽም፣ ከ78ሺሕ በላይ ምግብ ፈላጊ የወረዳው ነዋሪዎች የርዳታ እህል በመጠባበቅ ላይ ናቸው፤ ብለዋል።
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የዓይና ቡግና ከተማ ነዋሪዎች፣ የርዳታ እህል ወደሚከፋፈልበት ስፍራ በየቀኑ ቢሔዱም እህል እንዳላገኙ ነግረውናል።
ከዐማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽንና ከፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር እና ኮሚሽን መልስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ 03 ቀበሌ ቀጭኔ ተብሎ በሚጠራው ጎጥ፣ ትላንት ኀሙስ፣ የ54 አርሶ አደሮች ሰብል በቃጠሎ መውደሙን፣ የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ዛሬ አመሻሹን ለአሜሪካ ድምፅ ገልጿል። ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም